በመዲናዋ የአቅመ ደካሞች የምገባ ማዕከል ተመረቀ

ሚያዝያ 24/2013 (ዋልታ) –በአዲስ አበባ የመጀመሪያ የሆነውና ለአቅመ ደካሞች አገልግሎት የሚሰጠው የተስፋ ብርሀን ምገባ ማዕከል ተመረቀ::

አቅመ ደካሞችን ለመደገፍ በማለም በአምስት ክፍለ ከተሞች ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን ከእነዚህ ክፍለ ከተሞች መካከል የመጀመሪያው የምገባ ማዕከል በአራዳ ክፍለ ከተማ ተመርቆ ተከፍቷል።

ማዕከሉ በቀን ከ1ሺህ ለሚበልጡ አቅመ ደካሞች ዘላቂ የምገባ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ እና በትንሳኤ በዓል ላይ ተገኝተው ከአቅመ ደካምች ጋር በዓሉን ያሳለፋት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማችን በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ ዜጎች በርካቶች እንዳሉ በጥናት ተለይቶ የምገባ ማዕከል የማደራጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። ለዚህም ችግር
የተዳረጉ ዜጎችን ማገዝና መደገፍ ይኖርብናል ነው ያሉት።
ማዕከሉ እንዲገነባ ያደረጉ በጎ አድራጊዎችን አመስግነው ከተባበርን ሁሉን እንደምንሰራ ያመላከተ እንደሆነ አስታውቀዋል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሃና የሺንጉሴ የመጀመሪያው የምገባ ማዕከል ግንባታው በአንድ ወር የተጠናቀቀ መሆኑን ገልፀው፣ ከማዕከሉ ግንባታ መመልከት የሚቻለው ከተባበርን መስራት
እንደምንችል ነው ማሳያ ነው ብለዋል።
ማዕከሉ ለ28 ሰዎች የስራ እድል እንደፈጠረና ከ 1ሺህ በላይ የሚሆኑ አቅመ ደካማ ዜጎችን ተጠቃሚ
የሚያደርግ መሆኑንም አክለዋል።
በአምስቱ ክፍለ ከተሞች ተግባራዊ በሚደረገው የምገባ ማዕከላት ከ100ሺህ በላይ አቅመ ደካሞች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል።
(በሱራፌል መንግስቴ)