በምርጫ ሂደት ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን በመለየት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን መንግስት አስታወቀ

ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ

ግንቦት 02/2013 (ዋልታ) – በምርጫ ሂደት ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን በመለየት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን መንግስት አስታወቀ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው የፀጥታ ችግር በምርጫ እንቅስቃሴው ላይ እንከን መፍጠሩን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መንግስት የምርጫውን ሰላምና ጸጥታ ማረጋገጥ ዋንኛ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ ሲጠይቅ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር የምርጫ ቁሳቁሶችን ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የማጓጓዝ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው ለመስራት እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል።

በመሆኑም መንግስት ከቦርዱ ጋር በመነጋገር የጸጥታ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ በጋራ እየሰሩ በመሆኑን ዶክተር ቢቂላ ገልጸዋል።

በጸጥታ ችግር ምክንያት የመራጮች ምዝገባ ባልተጀመረባቸው አካበቢዎች የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ዜጎች በምርጫው ላይ ያለፀጥታ ስጋት ተሳትፎ እንዲያደርጉ መንግስት ሰላምና ጸጥታ ማስከበር ስራውን በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በ2013 ዓ.ም ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ መንግስት አገራዊ እቅድ አውጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድም የፖሊስና ደህንነት ተቋማትን ያቀፈ ብሔራዊ የደህንነት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በቅድመ ምርጫ ሂደት ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን በመለየት እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በምርጫ ዕለትና ከምርጫው በኋላ የግጭት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን የመለየትና የመተንተን ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ ተቋማት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ቢታዘቡ መልካም እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ቢቂላ የታዛቢዎቹ መቅረት በምርጫው ሂደት ላይ የሚያሳድረው ጉዳት እንደማይኖር ተናግረዋል።

ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርገው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ ሌላ የውጭ አካል አይደለምም ነው ያሉት።

ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ የጸጥታ ችግር ባለባቸው ቦታዎች ልዩ እቅድ እና ዝግጅት በማድረግ ከየክልሎቹ የጸጥታ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።