በምስራቅ ባሌ ዞን በፀሐይ ሀይል የተገነቡ 2 የኤሌክትሪክ ሀይል ማዕከላት ተመረቁ

ግንቦት 27/2013 (ዋልታ) – በምስራቅ ባሌ ለገሂዳ ወረዳ ቤልቱና ባህማ ከተሞች በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት “የብርሀን ለሁሉም” ፕሮጀክት የተገነቡ ሁለት የፀሐይ ሀይል ማዕከላት ዛሬ ተመርቀዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፣ የውሀ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንዲሁም ሌሎች የፌደራልና ክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

950 ኪሎዋት የኤሌክትሪከ ሃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው የማዕከላቱ ግንባታ የተካሄደው “ኖሪንኮ ኢንተርናሽናል” በተባለ የቻይና ስራ ተቋራጭ ነው።

ለማዕከላቱ ግንባታ ከዓለም ባንክ በተገኘ ከሰባት ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መሆኑን በምረቃው ስነ-ስርዓት ወቅት ተገልጿል።

ይህም ኢትዮጵያ ለጀመረችው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ተግባራዊነት በፀሀይ ሀይል የሚሰሩ 12 የፀሐይ ሀይል የኤሌክትሪክ ማዕከላት አካል እንደሆነ ተመልክቷል።

በፀሀይ ሀይል የሚሰሩት የኤሌክትሪክ ማመንጫ ማዕከላቱ የተገነቡት ከሀገሪቱ የሀይል ቋት በርቀት ላይ በሚገኙ ማህበረሰብ አካባቢዎች ነው ተብሏል።

የኤሌክትሪክ ማመንጫ ማዕከላቱ ከ20 ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ እንደሚያደርጉም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2025 ሁሉም ዜጎች የአገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡