በሰሜን ተራሮች ፓርክ ህገ-ወጥ የዱር እንስሳት አደንን ለመቆጣጠር የተሰራው ስራ ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ

መጋቢት 21/2013 (ዋልታ) – በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ይካሄድ የነበረውን ህገ-ወጥ የዱር እንስሳት አደን ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት ውጤት ማስገኘቱን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በጽህፈት ቤቱ የህብረተሰብና ቱሪዝም ኃላፊ ታደሰ ይግዛው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በፓርኩ በኢትዮጵያ ብቻ በሚገኙት ዋልያ፣ ቀይ ቀበሮና ጭላዳ ዝንጀሮዎች ላይ ይፈጸም የነበረውን ህገ-ወጥ አደን መቀነስ ተችሏል፡፡
የህብረሰቡን የባለቤትነት ስሜት በማጎልበት ከቱሪዝም ገቢው ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት በመከናወናቸው ህገ-ወጥ አደንን ለመቆጣጠር የተደረገው ጥረት ውጤታማ ነበር ብለዋል።
በዚህም በዋልያዎች ላይ የሚደርሰውን ሰው ሰራሽ ጉዳት መቀነስ ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የዋልያ አማካኝ የመኖሪያ እድሜ 15 ዓመት መድረሱንም ጠቁመዋል።
ቀደም ሲል በፓርኩ ውስጥ የዋልያዎችና ቀይ ቀበሮዎች ቁጥር ተመናምኖ እንደነበር አስታውሰው፤ ባለፉት ዓመታት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተከናወነው ስራ የዋልያዎች ቁጥር ከ700 እና የቀይ ቀበሮዎች ደግሞ ከ100 በላይ መድረሱን አስታውቀዋል።
“ባለፈው ሳምንት በፓርኩ ተከስቶ የነበረውን የእሳት ቃጠሎ የአካባቢው ህብረተሰብ ባደረገው ርብርብ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉ ህብረተሰቡ ለፓርኩ ያለውን ከፍ ያለ የባለቤትነት ስሜት ያረጋጋጠ ነው” ብለዋል፡፡
የደባርቅ ከተማ የኢኮ ቱሪዝም ህብረት ስራ ዩንየን ስራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ አየነው በበኩላቸው፤ በዩንየኑ አባላት ጥረትና ተሳትፎ በፓርኩ ህገ-ወጥ አደን ማስቀረት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡
“ከ8ሺህ በላይ የዩንየኑ አባላት ከቱሪዝም ገቢው ተጠቃሚ ናቸው” ያሉት ስራ-አስኪያጁ፤ የአባላቱ ህልውና በፓርኩ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ፓርኩን በመጠበቅ በኩል ተሳትፏቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።