በባህርዳር ከተማ በ400 ሚሊየን ብር የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ተጀመረ

ሰኔ 03/2013 (ዋልታ) – በባህርዳር ከተማ በ400 ሚሊየን ብር የ4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፓልት ኮንክሪት መንገዶች ግንባታ ተጀመረ።

በባህርዳር ከተማ በአጼ ቴዎድሮስና በአጼ ሚኒሊክ ክፍለ ከተሞች የሁለት መንገዶች ግንባታ በከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ተጀምሯል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በወቅቱ እንዳሉት አስተዳደሩ የከተማው ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ያነሷቸው የነበሩ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየሰራ ነው፡፡ “ግንባታቸው የተጀመሩ መንገዶችም የዚሁ ማሳያ ናቸው” ብለዋል።

በአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ከዳያስፖራ አስፓልት እስከ ዘንዘልማ 30 ሜትር ስፋት ያለው የ3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ግንባታ መጀመሩን አብስረዋል።

የመንገዱ ግንባታ ለአማራ መንገድ ስራዎች ድርጅት ባለስልጣን መሰጠቱንና በሁለት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።

በሚኒሊክ ክፍለ ከተማም ልደታ በሚባለው አካባቢ የአንድ ኪሎ ሜትር አስፓልት መንገድ  በቻይና ኩባንያ የሚገነባ መሆኑን ይፋ አድርገዋል።

የአስፓልት መንገዶቹ መገንባት የከተማውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከማፋጠን ባሻገር ገጽታውን ለማሻሻል እንደሚያስችል መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።