በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጤናው ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ የሚበረታታ ነው – ዶክተር ሊያ ታደሰ

ግንቦት 13/2013 (ዋልታ) – በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጤናው ዘርፍ የሚበረታታ ውጤት እየታየ መምጣቱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡
ዶክተር ሊያ በጉብኝታቸው ወቅት እንዳሉት፤ በገጠር የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ጤና ለማሻሻል እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት መልካም ናቸው፡፡
ሞዴል ቤተሰቦች በማብዛት የአጎበር እና መጸዳጃ ቤት አጠቃቀምን ጨምሮ ሌሎች የጤና ማሻሻያ ግብዓቶችን ህብረተሰቡ እንዲቀጠም የተከናወነው ውጤታማ ስራዎች መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለይ የአሶሳ ጤና ጣቢያ በውስጥ ገቢው የላቦራቶሪ እና የእናቶች ማቆያን በማጠናከር አገልግሎቱን ለማሻሻል ያደረገው ጥረት መልካም መሆኑን አመልክተዋል፡፡
እንደ ኢዜአ ዘገባ የአሶሳ ደም ባንክ እና የክልሉ መድሃኒት ኤጀንሲም የደም አቅርቦትን ጨምሮ ከከልሉ አልፈው አጎራባች ኦሮሚያ ክልል ጭምር መድሃኒት በማቅረብ ለህብረተቡ ጤና መጠበቅ ያሳዩት ቅንጅታዊ አሰራር ተስፋ ሰጪ ናቸው ብለዋል፡፡
በአንጻሩ የሚኒስቴሩን ድጋፍ የሚፈልጉ እና ብዙ መሻሻል ያለባቸው የጤና አገልግሎቶችም እንዳሉ ዶክተር ሊያ ተናግረዋል፡፡
ለእናቶች እና ህጻናት የሚሰጡት የነጻ አገልግሎቶች በተቋማቱ ላይ የፈጠሩት ጫናዎች መኖራቸውን ከጉብኝቱ መረዳታቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡
ሆኖም የነጻ የጤና አገልግሎቱ በማያስተጓጉል መልኩ በቀጣይ የጋራ ውይይት ተደርጎበት ማሻሻያ ሊደረግበት የሚችል አቅጣጫ እንደሚኖርም ገልጸዋል፡፡