በብራዚል በመጋቢት ወር ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 መሞታቸው ተገለጸ

መጋቢት 23/2013 (ዋልታ) – ብራዚል ውስጥ በፈረንጆቹ መጋቢት ወር ብቻ 66 ሺህ 570 ሰዎች በኮቪድ-19 ምክንያት መሞታቸውን ከአገሪቱ የወጡ መረጃዎች አመለከቱ።

ይህም ቀደም ካለው የካቲት ወር ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ የጨመረ መሆኑ ተነግሯል።

በአገሪቱ ኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች በጨመረ ቁጥር የጤና ተቋማት አቅም በእጅጉ እየተፈተነ መሆኑን ባለሙያዎች አስረድተዋል።

ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ የተህዋሲውን ወረርሽኝ የያዙበት መንገድ ከፍተኛ ትችት እና ነቀፌታን ያስከተለባቸው ሲሆን፣ በዚህ ሳምንትም አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ሥራውን በገዛ ፈቃዱ መልቀቁም ተገልጿል።

እንዲሁም በአገሪቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ አምስት የጤና ሚኒስትሮች ተቀያይረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ግን አሁንም የተለያዩ ግዛቶች አስተዳዳሪዎች እና ከንቲባዎች በሚያስተዳድሯቸው ከተሞች እና ግዛቶች ውስጥ የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት ያስቀመጡትን የእንቅስቃሴ ገደብ እየተቹ ነው።

“ያለን እና የነበረን ሁለት ጠላት ነው፤ ተህዋሲው እና ሥራ አጥነት! እውነታው ይህ ነው! ይህንን ደግሞ ቤት በመቀመጥ ልንቀርፈው አንችልም” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ብራዚል ረቡዕ ዕለት ተጨማሪ 3 ሺህ 800 ሰዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ሲሞቱ ከ90,000 በላይ አዳዲስ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አረጋግጣለች።

በብራዚል በኮቪድ-19 የሞቱ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር በዓለማችን በተህዋሲው ምክንያት የሞቱ ሰዎችን አንድ አራተኛ መያዙንም የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል።