በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ከሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ጋር ውይይት ተካሄደ

ታኅሣሥ 11/2014 (ዋልታ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ አገር ቤት የመመለስ ጥሪን በማስመልከት በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ ጽ/ቤት «ከዳያስፖራው ምን ይጠበቃል?» በሚል ርዕስ በስዊዘርላንድ፣ ኦስትሪያ፣ ሀንጋሪና ሩማንያ ከሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።
የጤና ሚኒስትር ዶክትር ሊያ ታደሰ፣ የዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እንድሪስ (ዶ/ር) እና የዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታምሩ ጊንበቶ በተሳተፉበት ውይይት ከአገራዊ ጥሪው ጋር በተያያዘ ለዳያስፖራ አባላቱ ወቅታዊ መረጃዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ ተሰጥቷል።
የዳያስፖራ አባላቱም ወቅታዊ መረጃን ከሚመለከተው አካል ለማግኘት የቻሉበት መድረክ በመመቻቸቱ መደሰታቸውን በመግለጽ፣ አገራቸውን ለማገዝ ያላቸውን ዝግጁነት መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመልክቷል።
በተያያዘ ዜናም በአሜሪካ ኮሎራዶና ሲያትል እንዲሁም በስዊዘርላንድ ጄኔቭና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የታላቁ ወደ ሀገር ቤት ጉዞን አስመልክቶና የተፈናቀሉ ወገኖችን መርዳት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ የበይነ መረብ ውይይት አካሂደዋል።