በታንዛኒያ ለታሰሩ ኢትዮጵያዊያን መፍትሄ ለማፈላለግ ስምምነት ተደረሰ

ግንቦት 4/2014 (ዋልታ) በታንዛኒያ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር ተያይዞ በእስር ላይ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የጋራ መፍትሄ ለማፈላለግ ሀገራቱ ከስምምነት ደረሱ፡፡
የታንዛኒያ ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮችን ያካተተ የልዑካን ቡድን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የለውጥ ሥራዎችን በመጎብኘት ውይይት አድርገዋል፡፡
ከፍተኛ አመራሮቹ በውይይታቸው ወቅት ስለ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በተለይ ኢትዮጵያዊ ወጣቶች በኬንያና በታንዛኒያ ሀገር አቋርጠው ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲጓዙ የሚያጋጥማቸውን አደጋና እንግልት በጋራ ለመቅረፍ የሚያስችል ተግባር ለማከናወን ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የአደገኛ እፅ ዝውውርን በጋራ ለመግታት፣ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ከታንዛኒያ ፖሊስ አካዳሚ ጋር በአቅም ግንባታ ላይ አብሮ ለመስራትና ከአንጋፋው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የተሻለ ልምድ እንዲሁም የታንዛኒያን ልምድ ለማካፈል ተስማምተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በተቋሙ እየተካሄደ ያለው የለውጥ ሥራ በወንጀል መከላከል፣ በምርመራና በቴክኖሎጂ ተቋሙ የደረሰበት ደረጃ ለልዑካን ቡድኑ ገለፃ አድርገውላቸዋል፡፡
የታንዛኒያ ፖሊስ ልዑክ መሪ ኢንስፔክተር ጄነራል ሲሞን ኞኮሮ ስሮ በጉብኝቱ ወቅት ስለተመለከቱት የለውጥ ሥራዎች ያላቸውን አድናቆት ገልፀው ለተደረገላቸው አቀባበልም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አንድ ቡድን ወደ ታንዛኒያ ሄዶ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር ተያይዞ በእስር ላይ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ ለመመልከትና ከእስር አስፈትቶ ወደ ሀገራቸው ለማስመለስ የሚያስችል የመፍትሄ ሀሳብ በጋራ ለማፈላለግ ስምምነት ላይ የተደረሰ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ እንዳመለከተው የሁለቱን ሀገራት የፖሊስ ግንኙነት ለማጠናከር የመግባቢያ ሰነድ በታንዛኒያ በመፈራረም የተጀመረውን ፖሊሳዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሁለቱ ሀገራት ፖሊስ ኃላፊዎች ተስማምተዋል፡፡
ለፈጣን መረጃዎች፦
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!