በትግራይ ክልል በሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት አሳስቦኛል አለ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን

ሐምሌ 06/2013 (ዋልታ) – የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ በትግራይ ክልል በሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት በእጅጉ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባ አሳሰቡ።

ኮሚሽነሩ በትግራይ ክልል የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ደህንነትን በተመለከተ በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህም በትግራይ ክልል የተካሄደው የሰላም ማስከበር ዘመቻ ከተጀመረ አንስቶ ስደተኞቹ በሁለት ተዋጊ አካላት መሃል ለመውደቅ መገደዳቸውን፣ ሁለት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች መውደማቸውን እና በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ሕይወታቸውን ለማትረፍ ዳግም ለመሰደድ መገደዳቸውን ገልጸዋል።
ኤርትራውያን ስደተኞች በአንድ ወይም ሌላ ወገን ደጋፊነት ተፈርጀው የበቀል ጥቃት እየደረሰባቸው እንዲሁም ተጠልፈው እየተወሰዱ እና እየተያዙ ስለመሆኑ የተጣሩ እና በማስረጃ የተደገፉ ሪፖርቶች ለኮሚሽኑ መድረሳቸውንም ተናግረዋል።
በማይ አይኒ እና በአዲ ሃሩሽ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በሚገኙ ስደተኞች ላይ በተለያዩ ታጣቂዎች በተለይ ማታ ማታ የሚፈፀሙ አጠቃላይ የወንጀል ድርጊቶች በእጅጉ ረብሸውኛል ብለዋል ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ።
ባለፉት ሳምንታት ሽሬ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ለእስር ተዳርገዋል ያሉት ኮሚሽነሩ፣ በመቐለ የሚገኙ አካላት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ እንዲሁም በሕገ-ወጥ መንገድ የታሰሩ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ መጠየቃቸውን ጠቁመዋል።
ከዚህም ባሻገር በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ በጣም ከባድ የሆኑ የኃይል ጥቃቶች እየደረሱ ስለመሆኑ የሚጠቁሙ ሪፖርቶች እየወጡ በመሆኑ፣ የፌደራል መንግሥትም ሆነ በትግራይ ክልል ያሉ አካላት በእነዚህ ተዓማኒ ክሶች ላይ መደበኛ ምርመራ እንዲጀምሩ ጥሪ ማቅረባቸውንም ገልጸዋል።
ስደተኞች ድጋፍ የሚሹ እና ዓለም አቀፍ ከለላ የማግኘት መብት ያላቸው ሲቪል በመሆናቸው በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የሚደርስው ጥቃት እና ማስፈራራት በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።