በአማራ ክልል ሲሰጥ የነበረው የ8ኛ ክፍል ፈተና መጠናቀቁ ተገለጸ

የ8ኛ ክፍል ፈተና በአማራ ክልል

ሰኔ 25/2013 (ዋልታ) – በአማራ ክልል ሲሰጥ የነበረው የ8ኛ ክፍል ፈተና በሰላም መጠናቀቁን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ የሰምንተኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ከሰኔ 23 እስከ 25/2013 ዓ.ም ሲሰጥ ሲሆን፣ በ5 ሺህ 521 ትምህርት ቤቶች ፈተናው ተሰጥቷል፡፡

ፈተናው በሰላም መጠናቀቁን በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ባለሙያና ተወካይ ቡድን መሪ ኃይሉ ታምር ተናግረዋል፡፡

ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ የጸጥታ አካላት፣ ባለሙያዎች፣ የሥራ ኃላፊዎችና ሕዝቡ ከፍተኛ አበርክቶ እንደነበራቸውም ገልጸዋል፡፡

በጠለምትና ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳዳር አንዳንድ አካባቢዎች ካለው የጸጥታ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ተማሪዎች በቂ ዝግጅት ባለማድረጋቸው ፈተናውን እንዳልወሰዱ አቶ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡

ፈተና ያልተሰጠባቸው አካባቢዎች በቀጣይ ከተለያዩ አካላት ጋር በመነጋገር ፈተናውን እንዲወስዱ ይደረጋል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡