በአማራ ክልል የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለማስተካከል ክልላዊ ማስፈፀሚያ እቅድ ተዘጋጅቶ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

መጋቢት 16/2013 (ዋልታ) – በክልሉ የተከሰተውን ከፍተኛ የዋጋ ንረት ለማስተካከል ክልላዊ ማስፈፀሚያ እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተዋቸው፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት 12 ሺህ 530 የሚደርሱ ድርጅቶች ላይ ፍተሻ ማድረጉን ገልጸው፣ ምርትን ያላግባብ ለብዙ ጊዜ አከማችተው የተገኙና መንግስት ያወጣውን የዋጋ ማስተካከያ ተግባራዊ ያላደረጉ 3 ሺህ 600 የሚደርሱ ድርጅቶች ታሽገዋል ብለዋል፡፡
እንዲሁም እስከ ትናንት ድረስ ገበያ ላይ መዋል ሲገባው ወደፊት የገበያው ዋጋ ይጨምራል በሚል መጋዘን ላይ አላግባብ ተከማችቶ የተገኘ ከ123 ሺህ ኩንታል በላይ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ማሽላ እና በርበሬ መገኘቱን አብራርተዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ 11 ሺህ 800 ኩንታሉን መንግስት ባወጣው ተመን መሠረት ለህብረተሠቡ ማከፋፈል መቻሉንና ቀሪው በቀጣይ ቀናት የሚከፋፈል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዛሬው ዕለት በባህር ዳር ከተማ የሚገኘው የመርከብ ዩኒየን የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር ስር ተከማችቶ የነበረ 2 ሺህ ኩንታል ጤፍ መንግስት ባወጣው ተመን መሰረት ለሸማቹ ህብረተሰብ ማከፋፈል መቻሉን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡