በአማራ ክልል የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ እንዲተገብር የክልሉ መንግስት ጠየቀ

ሐምሌ 27/2015 (ዋልታ) በአማራ ክልል ያጋጠመውን የፀጥታ መደፍረስ በመደበኛ የህግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ እንዲተገብር የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጠየቀ።

በአማራ ክልል የተከሰተው የሰላም መደፍረስ በክልሉ ከፍተኛ ሰብአዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እያደረሰ መሆኑን የክልሉ መንግስት አስታውቋል።

የተከሰተውን የፀጥታ ችግር በቁጥጥር ስር ለማዋል እስካሁን በክልሉና በፌደራል የፀጥታ ኃይሎች በኩል በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸው ይታወቃል።

ሆኖም በክልሉ ያለው የፀጥታ መደፍረስና ጥቃት በንፁሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በአስቸኳይ ለማስቆም የፌደራል መንግስት ከመደበኛው የህግ ማስከበር ሥርዓት ባሻገር በኢፌዴሪ ህገ መንግስት መሰረት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ በአፋጣኝ እንዲተገበር ነው የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የጠየቀው።

ክልሉ ወደ ቀደመ መረጋጋቱ እንዲመለስ ዜጎች ሰላማቸው ተመልሶ አርሶአደሩ ወደ እርሻው ክልሉም ወደ ልማት ስራዎች ፊቱን እንዲያዞር ለማድረግ መንግስት ያለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ ይገባልም በሚል የፌደራል መንግስትን ጠይቋል።