በአፍሪካ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ4 ሚሊየን አለፈ

መጋቢት 20/2013 (ዋልታ) – በአፍሪካ አህጉር የወረርሽኙ እየጨመረ መምጣት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር ከ4 ሚሊየን እንዲያልፍ ማድረጉን የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል (ሲዲሲ) ገለጸ።
በአፍሪካ ህብረት የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል (ሲዲሲ) እንዳስታወቀው እስካሁን ድረስ በአፍሪካ 4 ነጥብ 18 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎች በኮቪድ-19 ተይዘዋል።
ከነዚህ መካከል የ1 መቶ 11 ሺህ ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 3 ሚሊየን 743 ሺህ 4ቱ ደግሞ ከወረርሽኙ አገግመዋል።
ወረርሽኙ በደቡብ አፍሪካ ብቻ እስካሁን ድረስ የ 52 ሺህ 648 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።
የወረርሽኙ አሳሳቢነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ነው ሲዲሲ አፍርካ ያስታወቀው።
እንደ ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘገባ በበሽታው በከፍተኛ መጠን ከተጎዱ የአፍሪካ ሃገራት መካከል ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ግብጽ እና ሞሮኮ በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ደቡባዊ የአፍሪካ ክፍል በብዛት ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች አንዱ ሲሆን ሰሜናዊ እና ምስራቃዊ የአጉሪቱ አካባቢዎች ደግሞ ቀጥለው ተቀምጠዋል።
የአህጉሪቱ ማዕከላዊ ክፍል ደግሞ እምብዛም በወረርሽኙ ያልተጎዳ መሆኑም ተመልክቷል።
በዚህም የአፍሪካ አህጉር ኮቪድ-19 በአለም ካደረሰው ጉዳት 4.1 በመቶውን ይሸፍናል ተብሏል።
በኢትዮጰያ እስካሁን 200 ሺህ 563 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን 2 ሺህ 801 የሚሆኑት ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።