በኢትዮጵያ የአይሲቲ ተሰጥኦ ሥነ-ምህዳርን ለማልማት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

ሚያዝያ 04/2013 (ዋልታ) – የኢፌዴሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን እና በቴሌኮም መሠረተ ልማት ዋና አቅራቢነት የሚታወቀው ሁዋዌይ በኢትዮጵያ አይሲቲ ተሰጥኦ ሥነ ምህዳርን ለማልማት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

ሥነ ምህዳሩ ተማሪዎች እና ባለሙያዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የዕውቅና ማረጋገጫ እንዲያገኙ እና በቴሌኮም እና በአይቲ ዘርፍ የሚኖራችውን የወደፊት ጉዞ እንዲያዳብሩ የሚረዳ ነው ተብሏል።

ትብብሩ ሲተገበር የሁዋዌይ ሥልጠና እና የብቃት ማረጋገጫ አዳዲስ ተመራቂዎች ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ከማገዙም በላይ በኢንዱስትሪው ውስጥ ለሚገኙ ሥራ ፈጣሪዎች አዳዲስ ክህሎቶችን እንደሚያስገኝ ተገልጿል፡፡

በኮሚሽኑ የክህሎት ማዳበር እና የሥራ ፈጠራዋች ክትትል እንዲሁም የሥራ ስምሪት መርሃ ግብሮች አማካኝነትም በአገር ውስጥ ላለው የሥራ ኃይል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ዕውቅና እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡

የሥልጠናና የብቃት ማረጋገጫ መርሃግብሩ ለሶስት ዓመታት የሚቀጥል ሲሆን፣ በመጀመሪያው ዓመት ለ800፣ በሶስት ዓመታት ደግሞ ለ7ሺህ ወጣቶች የብቃት ማረጋገጫ ይሰጣል ተብሏል፡፡

ለ3 ሺህ ወጣቶች ሶስት ዓመታት በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ የሥራ ገበያ ውስጥ የሥራ ዕድሎችን የማመቻቸት እቅድ መያዙም ነው የተገለጸው።

በተጨማሪም በመጀመሪያ ዓመት 40 ዩኒቨርስቲዎች ላይ ግንዛቤን ለማሳደግ፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር፣ ሥልጠናዎችን እና የማዕከሉን ተመራቂዎች ቁጥር ለማሳደግ ያለመ ሲሆን፣ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ውስጥ 100 ዩኒቨርስቲዎችን እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማትን ለመሸፈን ያለመ መሆኑን ከኢፌዴሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡