በኬንያ አዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ተገኘ

በኬንያ አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ መገኘቱን ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያለው የሕክምና ምርምር ተቋም ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት አመለከተ።

ለኬንያ አዲስ የሆነው ዝርያው ከሰኔ ወር እስከ ጥቅምት ድረስ የተሰራን ጥናት ተከትሎ በደቡብ ምስራቅ የአገሪቷ ክፍል መገኘቱን የምርምር ተቋሙ አስታውቋል።

የቫይረሱ ዝርያ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ለማወቅ ተጨማሪ ምርምሮች እንደሚያስፈልጉም ተቋሙ አክሏል።

ተመራማሪዎች ቫይረስ ቅርፁን አሊያም ተፈጥሮን መቀየር የተለመደ እንደሆነ ይናገራሉ።

ኬንያ እስካሁን 100 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በኮቪድ-19 የተያዙ ሲሆን፣ ከ1 ሺህ 700 በላይ ሞት መዝግባለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡብ አፍሪካ በፍጥነት እየተዛመተ ያለው አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ በሦስት አፍሪካ አገራት መገኘቱ ተረጋግጧል።

እነዚህም ቦትስዋና፣ ዛምቢያ እና ጋምቢያ መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

በአፍሪካ እስካሁን በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 3 ሚሊዮየን የደረሰ ሲሆን፣ በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥርም በመጀመሪያው ዙር ወረርሽኝ ከነበረው የበለጠ ነው ተብሏል።

በአፍሪካ ከአውሮፓዊያኑ ታህሳስ 28 እስከ ጥር 10 ድረስ ባሉት ቀናት በአማካይ በቀን 25 ሺህ 223 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ተመዝግበዋል።

በአማካይ ከተመዘገበው 18 ሺህ 104 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ጋር ሲነፃፀር፤ አሁን ያለው ሥርጭት ከ39 በመቶ በላይ መብለጡን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

ድርጅቱ በወረርሽኙ ሳቢያ በጤና ተቋማት ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመከላከል የሕብረተሰብ ጤና የጥንቃቄ እርምጃዎች የበለጠ ወሳኝ መሆናቸውን ማሳሰቡን ቢቢሲ አስነብቧል።