በውጭ መገናኛ ብዙኃንና መንግሥታት ፊት ከፍ ያለው ታላቁ ግድብ

በሰለሞን በየነ

የካቲት 14/2014 (ዋልታ) ታላቁ የኅዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ኃይል ማመንጨት ሥራ በዓለም መገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶታል፡፡

በመጋቢት 24/2003 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦለት በዕለቱ ግንባታው የተጀመረውና ያልፉትን 11 ዓመታት ያለእረፍት የተደከመበት ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ ታላቅ ብሔራዊ ፕሮጀክት በመሆን በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ አፈፃፀሙ ዛሬ ላይ ከ84 ከመቶ እንዲሻገር ሆኗል፡፡

በሂደቱ በተለይም ከሦስትዮሽ ድርድሩ ጋር ተያይዞ ቀልብ ስቃዥ የሆነውና ከውጭ መገናኛ ብዙኃን ብሎም ከአገራትና መንግሥታት አጀንዳነት ዝቅ ብሎ የማያውቀው ግድቡ ኃያል ማመንጨቱን ተከትሎ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ሽፋን ሰጥተውል፡፡

በዚህም ከጉባ አስከ ኒውዮርኩ የፀጥታው ምክር ቤት የደረሰው የኢትዮጵያዊያኑ የዛሬ ዘመን ምልክቱ ግድብ የዓለም አጀንዳ በመሆን በዓለም መገናኛ ብዙኃን አርዕሰተ ዜና ጎልህ ስፍራ መያዝ ችሏል።

አልጀዚራ፣ ቢቢሲ እና ሮይተርስ በፊት ገጻቸው ባሰፈሩት ዘገባ “ኢትዮጵያ ከታላቁ የኅዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማምረት ጀመረች ሲሉ ሱዳንና ግብፅ ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ስጋት እንደሆነ ቢመለከቱትም ኢትዮጵያ ግን ለዕድገቷ አስፈላጊ እንደሆነ ትመለከተዋለች” ሲሉ አስነብበዋል። አክለውም በግድቡ ጉዳይ በግብጽና ሱዳን በኩል የሚነሱ አወዛጋቢ ጉዳዮች ቢኖሩም በብዙ ቢሊዮን ብር [ዶላር] ክስተቱ ለሚገመተው ፕሮጀክት አዲስ ምዕራፍ ከፋች እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡

የቱርኩ አናዶሉ በበኩሉ “ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የ5 ቢሊዮን ዶላር የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ሥራ ላይ ዋለ” ሲል ዘግቧል። የኃይል ማመንጨት ሥራውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳስጀመሩትና በመጀመሪያው ዙር 360 ሜጋ ዋት [ሥራ የጀመረው ተርባይን የሚያመነጨው ኃይል 375 ሜጋ ዋት ነው] እንደሚያመነጭ ጠቅሷል፡፡ ኢትዮጵያ እየገነባች የምትገኘው የኅዳሴ ግድብ “ነጩ ነዳጅ” ነው ሲልም ባሰፈረው የግንባታ፣ ተያያዥ ሂደቶችና ቀጣናዊ ነባራዊ ሁኔታ ትንታኔው ላይ አስፍሮታል፡፡

የመካከለኛው ምስራቅ የዜና ወኪል የሆነው ሚድል ኢስት ሞኒተር ባሰፈረው ዘገባ “ኢትዮጵያ ከታላቁ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማምረት ጀመረች” ሲል አስቀድሟል። አስከትሎም ሱዳንና ግብፅ ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ስጋት እንደሆነባቸው ቢመለከቱትም ኢትዮጵያ ግን ለዕድገቷ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ትመለከተዋለች ሲል ሮይተርስ ያሰፈውን መልዕክት በዜናው ላይ አክሏል፡፡

ዛሬም የጋራ ተጠቃሚነትን ለመቀበል ያልተዋጠላቸው የአረቡ ዓለም መገናኛ ብዙኃን ግን የግድቡ ኃይል ማመንጨትን በተመለከተ “በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል የተደረሰው የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት ተጣሰ” ሲሉ ያስተጋቡ ሲሆን ለዚህ ደግሞ የግብጹ አህራም ኦን-ላይን ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ ኃይል በማመንጨቷ የጣሰችው ሕግም ሆነ ስምምነት የለም።

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁ ኅዳሴ ግድብን መገንባት ስትጀምር ወንዙን በመጠቀም ልማቷን የማከናወን ተፈጥሯዊ መብቷን መጠቀምን በማለም ነበር፡፡

ሱዳን እና ግብጽ ሦስቱ አገራት በግድቡ ዙሪያ በሚያደርጉት ድርድር የኢትዮጵያን አካሄድ ይቀለብስልናል ብለው ባለሙት ልክ ለመፍታት በርካታ ድርድሮችን ተቀምጠዋል። አልፎም ከአፍሪካ ኅብረት ውጪ ሌሎች እንዲሳተፉ በተደጋጋሚ ሲወተውቱ ኢትዮጵያ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ርዕስ ሆኗ በመገናኛ ብዙኃኑም በተዛባ መልኩ ከእውነታዋ ያፈነገጡ ዘገባዎች ተላልፈው ነበር፡፡

ይህ ብቻ አይደለም ሁለቱ አገራት [ግብፅና ሱዳን] ጉዳዩን በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ከመውሰድ ጀምሮ አደራዳሪ እንዲኖር እስከመጠየቅ ሲደርሱም ኢትዮጵያ በዓለም መገናኛ ብዙኃን ሰፊ ዘመቻ ተከፍቶባት ነበር፡፡ ይሁንና ከጉባ አስከ ፀጥታው ምክር ቤት የደረሰው የዓባይ ውሃ ጉዳይ የደኅንነት ስጋት ሆኖ አንዲቀርብ ቢሞከርም የተሸረበው ሴራ በኢትዮጵያዊያንና ወዳጆቿ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ ሂደትን ተከትሎ የመጀመሪያውና ሁለተኛው የሙሌት ምዕራፍ በተከታታይ ዓመት ሲካሄድም የውጭ መገናኛ ብዙኃኑ በሳተላይት ጭምር በመከታተል ጉዳዩን በስጋት መልክ ሲያስቀምጡት ነበር።

ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ተሻግሮ የአፍሪካ ትልቁ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የሆነው የታለቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ጉባ ላይ የብርሃን ጮራውን ሲፈነጥቅ በጨለማ ውስጥ ለተቀመጡ ከ65 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን ተስፋ ሆኗል። የካቲት 13 ቀን 2014 የዓባይ ዘመን ልጆች ታሪክን በማይፋቅ ብዕር የከተቡበት ዕለት ሆኖ ተመዝግቧል።

በትውልድ ቅብብል ለድል እየበቃ ያለው የኅዳሴው ግድብ ግንባታ ሂደት እስካሁን ከ163 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን ይህም ከኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ኪስ እንጂ ከውጭ እርዳታ እና ድጋፍ የመጣ ድንቡሎ አለመኖሩን መንግሥት መሰረት ድንጋዩን ሲያስቀምጥ ጀምሮ ያሳወቀው ጉዳይ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የእነግብፅና የጥቅም ተጋሪ ሸሪኮቿ እጅ ከሚረዝምባቸው ዓለም ባንክና የዓለም ዐቀፉ ገንዘብ ተቋም ለግድቡ ግንባታ የሚውል ብድርና ዕርዳታ ማግኘት ስለማይታሰብም ጭምር ነው።

ያም አለ ይህ በመጋቢት 24/2003 ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ በኢትዮጵያዊያን ብርቱ ትጋድሎ ወደ መገባደዱ እየተጠጋ ሲሆን ግድቡ በሚጠናቀቅበት ወቅት በሚይዘው 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃና እሱ በሚፈጥረው ግዙፍ ሃይቅ ለኢትዮጵያዊያን ከመብራት ባሻገር የዓሣ ምርትና ቱሪዝም ማዕከል ለመሆን እየተንደረደረ ነው።