በደቡብ ክልል 13 ከተሞች የከተማ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ሊጀመር ነው

በደቡብ ክልል የከተማ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም

የካቲት 26/2013 (ዋልታ) – በደቡብ ክልል 13 ከተሞች የከተማ ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ሊጀመር እንደሆነ የክልሉ ኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ፕሮግራሙን በማስመልከት የፌደራል ከተሞች ስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በሀዋሳ ስልጠና ሰጥቷል።

የደቡብ ክልል ኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተሾመ ታከለ የየአካባቢውን ውስን ሀብት፣ የህዝቡን እውቀትና ጉልበት በማቀናጀት የከተማውን ህዝብ የምግብ ዋስትና ችግር መቅረፉ የወቅቱ ቁልፍ ጥያቄ ነው ብለዋል።

ለዚህ ፕሮግራም ስኬት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅትና በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ያሉት አቶ ተሾመ፣ ቢሮው ጠንካራ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

በክልሉ ይህን የህዝብ ችግር ለመቅረፍ ራሱን የቻለ ኤጀንሲና በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ የከተማ ምግብ ዋስትናና የስራ እድል ፈጠራ ምክር ቤት መቋቋሙን ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል የከተማ ምግብ ዋስትናና ስራ እድል ፈጠራ ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ አቶ ማርቆስ ቡልቻ፣ የከተማ ምግብ ዋስትና ፕሮግራሙ በዚህ አመት ከመጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ በ13ቱ ከተሞች ይተገበራል ብለዋል።

በፌደራል ከተሞች የስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የማህበረሰብ ተሳትፎ ዳይሬክተር ወ/ሮ አስቴር ሰይፉ፣ ለፕሮግራሙ ስኬት ህዝቡና የአመራር አካላት ተቀናጅተው እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ማቅረባቸዉን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡