በጀርመን ስቱትጋርት ለሕዳሴ ግድብ ከ6 ሺህ 200 ዩሮ በላይ ተሰበሰበ

ሐምሌ 26/2013(ዋልታ) – በጀርመን የስቱትጋርት ኢትዮ ብሪጅ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አዘጋጅነት በከተማዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቦንድ እና የመጽሔት ሽያጭ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

በፕሮግራሙ ላይ ከኢትዮጵያውያኑ እና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በቦንድ እና መጽሔት ሽያጭ ከ6 ሺህ 200 ዩሮ በላይ ገቢ ተሰብስቧል፤ በቀጣይም ከ2000 ሺህ በላይ የሕዳሴ መጽሔት ለማከፋፈል ቃል ተገብቷል።

በተጨማሪም ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ሦስት አባላት ያሉት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ተቋቁሟል።

በሌላ በኩል የዳያስፖራ አባላቱ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስከበር የሚያደርገውን ፍልሚያ እንደግፋለን ያሉ ሲሆን በቀጣይም ለሠራዊቱ ድጋፍ ለማሰባሰብ አስተባባሪ ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡

በጀርመን ፍራንክፈርት የኢፌዴሪ ቆንስል ጄነራል አቶ ፈቃዱ በየነ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ዳያስፖራው ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ በማድረግም ሆነ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም የሀገር አለኝታነቱን እንዲያሳይ ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።