በጊኒ ኢቦላ ተቀስቅሶ ሦስት ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ

በጊኒ ኢቦላ ተቀስቅሶ 3 ሰዎች ሲሞቱ፣ ሌሎች አራት ሰዎች ደግሞ ተቅማጥ፣ ማስመለስና የመድማት ምልክቶችን እያሳዩ እንደሆነ ተገልጿል።

አራቱ ሰዎች እነዚህን ምልክቶች ማሳየት የጀመሩት የአንድ በኢቦላ የሞተችን ነርስ ቀብር ከታደሙ በኋላ ነበር።

በፈረንጆቹ ከ2013 እስከ 2016 ብቻ በምዕራብ አፍሪካ ኢቦላ ወረርሽኝ የ11ሺህ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።

ወረርሽኙ ጊኒን ጨምሮ ጎረቤቶቿን ላይቤሪያንና ሴራሊዮንን በከፍተኛ ሁኔታ አጥቅቶ የነበር ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም በርካታ ክትባቶች ተሞክረዋል። ክትባቶቹ ወረርሽኞቹን ለማቆም በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ አገልግሎት ላይ ሲውሉ እንደነበርም  ተጠቁሟል።

የዓለም ጤና ድርጅት የጊኒ ተወካይ አልፍሬድ ጆርጅ ኪ ዜርቦ “አስፈላጊውን ክትባት ለማቅረብ የዓለም ጤና ድርጅት ከመድኃኒት አምራቾች ጋር እየተነጋገረ ነው ብለዋል።

የኢቦላ ክትባት ለመጀመርያ ጊዜ በ2015 በጊኒ ሙከራ ተደርጎ ውጤት ማስገኘቱ ይታወሳል። ከክትባቱ ሌላ ታማሚው የመዳን እድሉን የሚጨምሩ መድኃኒቶች መፈብረካቸውም ይታወቃል።

ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈውም በደም፣ በሰውነት ፈሳሽ ወይም ተህዋሲው ከነካው አካባቢ ሊሆን ይችላል። አሁን ሁሉም በተህዋሲው የተያዙት እድሜያቸው ከ25 ዓመት በላይ የሆኑና የነርሷን ቀብር የታደሙት ናቸው።

የወረርሽኙን መቀስቀስ ተከትሎ ሴራሊዮንና ላይቤሪያ በተጠንቀቅ ላይ ይገኛሉ። የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃ ለጤና ሚኒስትሮቻቸው ጉዳዩን በንቃት እንዲከታተሉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ኢቦላ ተህዋሲ ድንገቴ ትኩሳት በመፍጠር በአጭር ሰዓት ታማሚውን በማዳከም የጡንቻ ከባድ ሕመም ፈጥሮ ጉሮሮን አቁሱሎ የሚገድል በሽታ ነው።

ከዚህም ባሻገር ማስመለስ፣ ማስቀመጥ እና የውስጥና የውጭ መድማትን ያስከትላል።

ታማሚዎች የሚሞቱት ብዙውን ጊዜ ፈሳሽ ከሰውነታቸው ተሟጦ ስለሚያልቅ ነው፡፡

(ምንጭ፡-ቢቢሲ)