በጋምቤላ ኢታንግ ልዩ ወረዳ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውር የተገኘ ግለሰብ በቀጥጥር ስር ዋለ

በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውር የተገኘ ግለሰብ በቁጥጥር ስራ መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ኮማንደር ኡማን ኡጋላ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቡ በቀጥጥር ስር የዋለው ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠረፍ ከሚገኘው ዋንተዋር ወረዳን አቋርጦ ወደ ኢታንግ ልዩ ወረዳ ጦር መሳሪያዎችን በሸክም ለማስገባት ሲሞክር ነው።

የጦር መሳሪያዎቹ  አምስት ታጣፊና ሁለት  ባለሰደፍ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ግለሰቡ በተጠርጣሪነት ተይዞ ተጨማሪ የማጣራት ሥራው እንደተጠናቀቀም ጉዳዩ ለፍርድ ቤት ይላካል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር ባደረገው ጥረት 352 የክላሽንኮቭ ጠብንጃዎች እና ከአንድ ሺህ 870 በላይ  ተተኳሽ ጥይቶች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ኮማንደር ኡማን አስታውሰዋል።

በጦር መሳሪያ አዘዋዋሪነት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት 12 ግለሰቦች መካከልም በአምስቱ ላይ ከስምንት እስከ አስር ዓመት የሚደርስ የእስራት ቅጣት እንደተወሰነባቸውና የቀሪዎቹ ጉዳይም በፍርድ ቤት በሂደት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

የክልሉ ህዝብ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ የሚያደርሰውን ጉዳት  በመገንዘቡ ባለፉት ስድስት ወራት ይህንን  በመቆጣጠር ረገድ ድጋፍ  ማድረጉን ም ጠቁመዋል።

በቀጣይም የጦር መሳሪያ ዝውውሩን ለመግታት በሚደረገው ጥረት ህዝቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮሚሽነሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።