በጋምቤላ ከተማ የ10 ዓመታት መሪ የልማት እቅድ ላይ የክልሉ አመራሮች እና ባለሙያዎች ምክክር አደረ

በጋምቤላ ክልል በቀጣይ 10 ዓመታት ውስጥ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያለመ እቅድ መዘጋጀቱን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።

በክልሉ የአሥር ዓመት መሪ የልማት እቅድ ላይ የክልሉ አመራሮች እና ባለሙያዎች በጋምቤላ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

ርእሰ መስተዳድሩ በክልሉ ከ2003 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ በሁለት የእቅድ እና ትራንስፎርሜሽን ዘመናት በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በመጀመሪያው እና ሁለተኛው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በኢኮኖሚ እድገት፣ በመሠረተ ልማት፣ በማኅበራዊ ልማት እና በአቅም ግንባታ ዙሪያ ቀጣይነት ያላቸው ስኬታማ አፈጻጸሞች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።

ባለፉት ዓመታት በክልሉ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ፣ የሥራ እድል በመፍጠር እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ርብርብ የተደረገ ቢሆንም፣ ሰፊ የሥራ እድል ከመፍጠር አንጻር ውስንነቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በቀጣይ አስር ዓመታት ውስጥ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያለመ እቅድ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

ባለፉት ሁለት የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዓመታት የተመዘገቡ መልካም ተሞክሮዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል በቀጣይ አሥር ዓመታት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የክልሉ ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሓላፊ አቶ ኡቦንግ ኡቶው በበኩላቸው፣ በክልሉ ባለፉት የእቅድ ትግበራ ዓመታት የተገኙ ጥንካሬዎች እና መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት በቀጣይ አሥር ዓመታት በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።

በመድረኩ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የፋይናንስ ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ከጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።