በፈረንሳይ በተካሄደ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች አትሌቶቻችን ድል አስመዘገቡ

ሰኔ 29/2013 (ዋልታ) – በሳምንቱ መጨረሻ በፈረንሳይ በተካሄደ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች አትሌቶቻችን አበረታች ውጤቶችን አስመዝግበዋል።

በዚህም በፈረንሳይ፣ ሌንስ በተካሄደ የ5 ኪሎ ሜትር ውድድር ያሲን ሃጂ በ13 ደቂቃ ከ18 ሰከንድ በመግባት ውድድሩን በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ፣ ጥላሁን ኃይሌ በ13 ደቂቃ 32 ሰከንድ በመግባት ውድድሩን በሁለተኝነት አጠናቋል።

በ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ወንዶች ደግሞ አንተናየሁ ዳኛቸው በ29 ደቂቃ 04 ሰክንድ በመግባት ውድድሩን በሶስተኝነት ሲያጠናቅቅ በዚሁ በ10 ኪሎ ሜትር የሴቶች ውድድር ደግሞ አዲሴ ምስለኔው በ31 ደቂቃ ከ49 ሰክንድ በመግባት ውድድሯን  በሁለተኛነት አጠናቃለች።

በተጨማሪም በፈረንሳይ ሌንስ በተካሄደ የግማሽ ማራቶን ውድድር በወንዶች አቤል ጥላሁን  በ1 ሰዓት 25 ሰከንድ በአራተኛነት ውድድሩን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ በሴቶች ደግሞ ጎይተቶም ገ/ስላሴ በ1 ሰዓት ከ7 ደቂቃ 52 ሰከንድ በ3ኛነት ውድድሯን ማጠናቀቋን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።