በ350 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የቦረና ዩኒቨርሲቲ ተመረቀ

ሰኔ 04/2013 (ዋልታ) – የከፍተኛ ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ በ350 ሚሊየን ብር ወጪ በ50 ሔክታር መሬት ላይ የተገነባው የቦረና ዩኒቨርሲቲ ተመረቀ፡፡

በምርቃት ሥነሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ የቦረና ዩኒቨርሲቲ ከቦረና ህዝብ በተጨማሪ የልማት ተጠቃሚ ላልሆኑ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች በረከት መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የኦሮሞን ህዝብ አንድነት ማጠናከር የአፍሪካ ቀንድ ክልልን አንድነት ማጠናከር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ ለዚህም መንግስት በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር አከባቢ የተለያዩ የልማት ስራዎችን እየሰራ ነው ብለዋል።

በምርቃት ሥነሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኬንያ መርሰቤት ካውንቲ ገዢ ኢንጅነር መሃመድ አሊ የቦረና ዩኒቨርሲቲ በሁለቱም ሀገራት የሚኖሩ የቦረና ኦሮሞን ለማቀራረብ እና በጋራ ለማበልፀግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የመማሪያ ክፍሎች፣ የአስተዳደር ቢሮዎች፣ ቤተ ሙከራ፣ ቤተ መጽሐፍት፣ አዳራሽና  የስፖርት ማዘውተሪያን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪ ለትምህርት ስራ አገልግሎት የሚውሉ ሌሎችም ግብዓቶች የተሟሉበት ዩኒቨርሲቲ ነውም ተብሏል፡፡

ዩኒቨርስቲው ለዓመታት የዘለቀ የአርብቶ አደሩን ጥያቄ የመለሰ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ምርቃት መርኃግብር የክልሉ ፕሬዝዳንት ሺመልስ አብዲሳ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) እንዲሁም የተለያዩ የፌዴራልና የክልል የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በመርኃግብሩ ለዩኒቨርሲቲው መመስረት ትልቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም እውቅና ተበርክቶላቸዋል።

(በሶሬቻ ቀበኔቻ)