ባለሃብቶች ለገበታ ለሃገር የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑ ተገለጸ

ባለሃብቶች ለገበታ ለሃገር ፕሮጀክቶች የተጠናከረ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ብሔራዊ ሐብት አሰባሳቢ ኮሚቴው አስታወቀ።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚዘጋጀው የማጠቃለያ  የዕራት መርሃ ግብር በቀጣዩ ሣምንት እንደሚካሄድ ተገልጿል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራው ብሔራዊ ኮሚቴ አባልና የባለሃብቶች አስተባባሪ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ለኢዜአ እንደገለጹት ኮይሻ፣ ጎርጎራና ወንጪ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር የሃብት ማሰባሰብ መርሃ ግብር እየተከናወነ ነው።

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚለሙት ሶስቱ ፕሮጀክቶች የክልሎችን፣ የከተማና የቱሪዝም ልማትን ለማስፋት ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኒሼቲቭ የሆኑትን ፕሮጀክቶች ስራ ለማስጀመር እየተካሄደ ባለው የሃብት ማሰባሰብ በሁሉም ዘርፍ ያለው የቢዝነስ ማኅበረሰብ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የግሉ ዘርፍ ከጅምሩ ያሳየው ምላሽ አዎንታዊ መሆኑን ያወሱት አምባሳደር ምስጋኑ በሸገር ፕሮጀክቶች የነበረው ተሳትፎና ድጋፍ ለገበታ ለሃገርም ተጠናክሮ መቀጠሉን አብራርተዋል።

በቀጣዩ ሣምንት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የማጠቃለያ የዕራት መርሃ ግብር እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።

በመርሃ ግብሩ ለመሳተፍ በቪአይፒ 5 ሚሊዮን ብር በቪቪአይፒ ደግሞ 10 ሚሊዮን ብር ሲሆን በርካታ ባለሃብቶች ገንዘቡን ገቢ እያደረጉና ቃል እየገቡም ነው ብለዋል።

ቃል የገቡ ባለሃብቶች በቀሪዎቹ ቀናት ቃላቸውን በመፈጸም በመርሃ ግብሩ ተሳታፊ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሮጀክቶቹ ዓለም አቀፍ ቱሪዝምና ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የስራ ዕድል በመፍጠርና ለባለሃብቱም ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታም አብራርተዋል።

አዳዲስ ሃብት በመፍጠርና የቢዝነስ ሞዴሎችን በማምጣት ለባለሃብቱ ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የመሳተፍ ዕድል ይዘው ይመጣሉ ብለዋል።

ባለሃብቱ በአገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በሚሊዮኖች በሚቆጠር ገንዘብ አስተዋጽኦ በማድረግ መሳተፉ አዲስ ጅማሬ በመሆኑ የበለጠ እንዲሳተፍ ምቹ ሁኔታዎችን መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቶቹ ኢትዮጵያን በትብብር በማልማት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመፍጠር እሳቤን ለማሳካት ተምሳሌት መሆናቸውን አምባሳደር ምስጋኑ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የብሔራዊ ቤተ-መንግስት፣ ወዳጅነት ፓርክ፣ እንጦጦና መስቀል አደባባይ ፕሮጀክቶች በስኬት መጠናቀቃቸው ለከተማዋና ለአገሪቷም አዳዲስ ዕድሎች፣ ልምዶች፣ የቢዝነስ ሃሳቦችና እሴቶችን ይዘው መምጣታቸውን አውስተዋል።

ፕሮጀክቶቹ አንድነትን፣ ብሔራዊ መግባባትን፣ የጋራ ልማትና አብሮነትን የሚያስተሳስሩ በመሆናቸው ለስኬታማነታቸው ሁሉም በሚችለው ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።