ባይደን እስራኤል እና ፍልስጤም የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጠየቁ

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

ግንቦት 10/2013 (ዋልታ) – የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በእስራኤል እና በፍልስጤም ሚሊሻዎች መካከል ለስምንት ቀናት ያክል በጋዛ የቀጠለው ግጭት እንዲቆም ሁለቱ ኃይሎች የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጠየቁ።

ባይደን ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ከግብጽ እና ሌሎች አገራት ጋር በመሆን የሁለቱን አገራት ጠብ ጋብ ለማድረግ እየሰሩ እንደሆነም ነግረዋቸዋል፡፡

አሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በሁለቱ አገራት መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሊያወጣው የነበረውን መግለጫ ባለመስማማቷ አስቁማለች።

ለሁለት ሳምንታት የዘለቀው ግጭት እስካሁን ድረስ 61 ህፃናትን ጨምሮ የ212 ሰዎችን ህይወት በጋዛ ቀጥፏል። እስራኤል ደግሞ 10 ሰዎች ሲሞቱባት ሁለቱ ህፃናት መሆናቸው ተጠቁሟል።

እስራኤል በጋዛ ተዋጊዎችን ብቻ ነው የገደልኩት ማለቷን የቀጠለች ሲሆን፣ የሲቪል ሰዎች ሞት ካለ እንኳን ሆን ብዬ አይደለም ብላለች። ሃማስ ግን ይህንን ይቃወማል።

“ባይደን የሲቪል ሰዎችን ደህንነት ለመጠበቅ እስራኤልን አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት እንድታደርግ አበረታተዋል” ሲል የነጩ ቤተ መንግሥት መግለጫ አስነብቧል።

“ሁለቱ መሪዎች ሃማስ እና ሌሎች የአሸባሪ ድርጅቶች ላይ የእስራኤል ወታደራዊ ኦፕሬሽኖችን በተመለከተ ውይይት አድርገዋል” ሲልም አክሏል።

በግጭቱ ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ስጋቱን እየገለፀ ሲሆን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም የሲቪል ሰዎች ሞት እና የግንባታዎች ብሎም የመሰረተ ልማት መውደም እንዲቆም ግልፅ ጥሪዎች እያደረጉ ይገኛሉ።

የፀጥታው ምክር ቤት እስራኤል የምታካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ እንድታቆም እና ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄዎችን እንድትከተል የሚጠይቀው የተኩስ አቁም ጥሪ መግለጫን አሜሪካ ስታስቆም ይህ ለሶስተኛ ግዜ ነው ተብሏል።

“የኛ ስሌት ይህንን ውይይት ከጀርባ ማካሄድ ነው። እስካሁን ልንወስደው የምንችለው ያለንን ገንቢ አማራጭ ነው” ሲሉ የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።