ብራዚል በአንድ ቀን 4ሺህ ዜጎቿን በኮሮናቫይረስ አጣች

መጋቢት 29/2013 (ዋልታ) – ብራዚል ለመጀመርያ ጊዜ በ24 ሰዓታት ውስጥ 4ሺህ ሰዎች በኮሮና ምክንያት መሞታቸውን ይፋ አደረገች፡፡

ለዚህም እንደ ምክንያት አዲሱ ዓይነት የኮቪድ ተህዋሲ ዝርያ መከሰቱ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በብራዚል ሆስፒታሎች ከሚችሉት ታማሚ በላይ እያስታመሙ ሲሆን፣ በአንዳንድ ከተሞች ሰዎች አልጋ ወረፋ እየተጠባበቁ ተራ ሳይደርሳቸው እየሞቱ ናቸው ተብሏል፡፡ የሰው ሰራሽ መተንፈሻ መሣሪያዎች እጥረትም ተከስቷል፡፡

ወረርሽኙ ከመጣ ወዲህ ብራዚል የሞቱባት ዜጎች ቁጥር 337 ሺህ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም በዓለም ከአሜሪካ ቀጥሎ ሁለተኛው አስፈሪ ቁጥር ነው፡፡ በአሜሪካ ከግማሽ ሚሊየን ዜጎች በላይ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ ይህ ሁሉ ዜጋ ሞቶባቸውም ዘጋግቶ ቤት የመቀመጥ እርምጃን መቃወማቸው ተጠቁሟል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት ዜጎች ከቤት እንዳይወጡ ቢደረግ የምጣኔ ሀብት ቀውስና መዘዙ ከኮቪድ-19 የባሰ ሕዝቡን ይጨርሳል፡፡

ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ ባለፈው ማክሰኞ ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ባደረጉ ጊዜ የእንቅስቃሴ ገደብ ያስቀመጡ የክልል ገዢዎችን ወቅሰዋል፡፡

‹‹ቤት መቀመጥ ትርፉ መወፈርና ድብርት ነው፤ ቤት መቀመጥ ትርፉ የሥራ አጥ ቁጥርን ማብዛት ነው›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በዚህ ንግግራቸው እሳቸው በሚመሯት ብራዚል በ24 ሰዓታት 4ሺህ ዜጎች የመሞታቸውን ነገር ሳያነሱ አልፈውታል፡፡

በብራዚል እስከዛሬ በተህዋሲው የተያዙት ሰዎች ቁጥር 13 ሚሊየን ያለፈ ሲሆን፣ በመጋቢት ወር ብቻ 66 ሺህ ዜጎች ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ማለፉን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል፡፡