ቦርዱ በምርጫ ሂደት የሴቶችን ተሣትፎ ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥልጠና ለምርጫ ታዛቢዎች ሰጠ

ብዙወርቅ ከተተ

ሚያዝያ 04/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ሂደት ውስጥ የሴቶችን ተሣትፎ ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥልጠና ለምርጫ ታዛቢዎች ለሶስት ቀናት ሰጠ፡፡

በሥልጠናው ወቅት የቦርዱ አመራር የሆኑት ብዙወርቅ ከተተ ባደረጉት ንግግር የቦርዱ የሥርዓተ ፆታና ማኅበራዊ አካታችነት ክፍል ኃላፊ አማካኝነት የ6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ አካታች ለማድረግ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እየተተገበሩ ያሉ ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን አብራርተዋል።

ምርጫን ለመታዘብ ሥርዓተ-ፆታ የሚያስፈልግባቸው ምክንያቶችና የሚካተቱበት አግባብነት፣ በምርጫው ዑደት ውስጥ በሁሉም ደረጃዎች ሥርዓተ-ፆታን ያማከለ የምርጫ መታዘብ፣ በምርጫ ሂደት ውስጥ የሴቶችን ተሣትፎ እና የፆታ እኩልነት የሚመለከት የሕግ ማዕቀፍ በኢትዮጵያ፣ በምርጫ ወቅት ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ዓይነት፣ በዓለም ዐቀፍና በሀገር ዐቀፍ ደረጃ የሴቶች ተሣትፎ እንቅፋቶች ሥልጠናው ካካተታቸው አጀንዳዎች ውስጥ ይገኙበታል።

በሥልጠናው መጠናቀቂያ ላይ የቦርዱ የሥርዓተ-ፆታና ማኅበራዊ አካታችነት ክፍል ኃላፊዋ ለተሣታፊዎቹ የተሣትፎ የምስክር ወረቀት የሰጡ ሲሆን፣ ታዛቢዎቹ በምርጫው ሂደት ውስጥ የሚኖራቸው ተሣትፎ የሴቶችን እና ትኩረት የሚሹ ዜጎችን አካታችነት በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲሆን መሳሰባቸውን ከቦርዱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።