ተስፋ የተጣለባቸው ታዳጊ ተጫዋቾች


በዋና አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በታንዛንያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የሴካፋ ዞን ከ20 ዓመት በታች አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ውድድር ዝግጅቱን እያከናወነ ይገኛል።

አሰልጣኙ ለተጫዋቾች ጥሪ አድርገው በአበበ ቢቂላ ስታዲዬም ልምምድ እያደረጉ ሲሆን ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች ውስጥ ታዳጊዎቹ ናትናኤል አረጋዊና ቢኒያም ደስታው ይገኙበታል።

እነዚህ ሁለቱ የ18 ዓመት ታዳጊዎች ቲኤፍኤ በሚባል በዱባይ ሊግ በሶስተኛ ዲቪዚዮን በሚወዳደር የእግር ኳስ ቡድን አካዳሚ ውስጥ የሚጫወቱ ታዳጊ እግር ኳስ ተጫዋቾች ናቸው።

ከባህር ዳር የተገኘው ቢኒያም የመሃል ሜዳ ተጫዋች ሲሆን በአካዳሚው የተስፋ (ሁለተኛው) ቡድን ውስጥ ተጫዋች ነው። ናትናኤል አረጋዊ በበኩሉ በዋናው ቡድን ውስጥ በመግባት የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጓል።

ሁለቱም ታዳጊዎች በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የስፖርት ፕሮጀክቶችና አካዳሚዎች መሰልጠናቸውንና በአሰልጣኝ እድሉ ደረጄ በሚመራው ኢዲዋይ አካዳሚ በኩል ወደ ዱባዩ እግር ኳስ ቡድን አካዳሚ ለመግባት እንደቻሉ ከአዲስ ዋልታ ዲጂታል ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ በኋላም በባህር ዳር ከነማ ተስፋ ቡድን የሰለጠነው ቢኒያም አዲስ አበባ በመምጣት በኢዲዋይ አካዳሚ ሙከራ አድርጎ ከ200 ሰልጣኞች መካከል ተመርጦ ወደ ዱባይ ለመጓዝ ችሏል።

ቢኒያም በዱባይ ያገኘውን ሥልጠና ሲገልጽ በአካል ብቃት፣ በቴክኒክና በታክቲክ ላይ በትኩረት ስለሚሰሩ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጣ አስችሎኛል ብሏል።

በግራና በቀኝ ክንፍ የሚጫወተው ናትናኤል አረጋዊ በበኩሉ ቀጫጫና አጭር በመሆኔ በአገር ውስጥ ቡድኖች ለመጫወት ያደረኩት ሙከራ ተስፋ አስቆራጭ ነበር ብሏል፡፡ ነገር ግን የዱባዩ ቲኤፍኤ መጀመሪያ የሚያዩት ችሎታን ወይም ታለንት እንደሆነና በሙከራ ወቅት ችሎታውን ስላዩ ለ30 ቀን ሙከራ ወደ ዱባይ አቅንቶ ለተስፋ ቡድኑ መፈረሙን ተናግሯል። ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ደግሞ ለዋናው ቡድን መፈረሙን ገልጿል።

“እዛ ሁሉ ነገር የተሟላ ነው፤ አቅምን ማውጣት ነው ካንተ የሚጠበቀው” የሚለው ናትናኤል እድሉን ቢያገኙ ከእርሱ የሚበልጡ ታለንት ያላቸው ታዳጊ ኢትዮጵያዊያን የእግር ኳስ ተጫዋቾች መኖራቸውን ይናገራል።

የኢዲዋይ አካዳሚ ባለቤት አሰልጣኝ እድሉ ደረጄ የልጆቹን ለብሔራዊ ቡድን መጠራት አስመልክቶ ሲገልፅ “አሁን የተመረጡት ተጫዋቾች ጥሩ አቅም ካሳዩ ከቡድኑ ጋር ወደ ታንዛኒያ ከተጓዙ፣ አንድ ነገር ነው። ሁለተኛም መጠራታቸው ራሱ ትልቅ ነገር ነው። ካላቸው አቅም አንጻር ሀገራቸውን ይጠቅማሉ ብዬ አስባለሁም” ብሏል።

አካዳሚዎቹ በትብብር መስራታቸው እና በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በውጭ ለሚጫወቱ ተጫዋቾች ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ተጠርተው የሚጫወቱበትን ሁኔታዎች ማመቻቸቱ ወጣቶቹ ለብሔራዊ ቡድን እንዲመረጡ አስተዋፅኦ ማድረጉን አሰልጣኝ እድሉ ይጠቅሳል።

ወጣት እግር ኳስ ተጫዋቾችን ለዓለም አቀፍ እግር ኳስ አሰራሮችና አሰለጣጠኖች ተጠቃሚ በማድረግ ለአውሮፓ ሊጎች የመጫወት እድል እንዲፈጠርላቸው በመካከለኛው ምስራቅ ካሉ አካዳሚዎችም ጋር መስራት ጥሩ አማራጭ መሆኑን አሰልጣኙ ተናግሯል።

በሳይንሳዊ አሰለጣጠን፣ በታክቲክና ቴክኒክ እንዲሁም በተደራጁ የእግር ኳስ አካዳሚዎች ውስጥ ያለፉ ወጣት የእግር ኳስ ተጫዋቾች የአገራችንን እግር ኳስ ፕሮፌሽናሊዝም እድገት ከፍ በማድረግና የዕውቀት ሽግግር በማድረግ ከፍ ያለ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ይታመናል።

በቴዎድሮስ ሳህለ