ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በትብብር እየተሰራ መሆኑ ተጠቆመ

ሰኔ 04/2013 (ዋልታ) – በተለያየ ጊዜ ከክልሉና ከሌሎች አካባቢዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በትብብር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ደቡብ ወሎ ዞን ኩታበር ከተማ በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ዛሬ ጎብኝተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝቱ በወቅት እንደገለፁት፣ ለ27 ዓመታት በተሰራ የተሳሳተ ትርክት ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች እንዲፈናቀሉና ችግር ውስጥ እንዲወድቁ ተደርጓል።

ከክልሉ ውጭ የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ከተለያዩ የክልል ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

ከኦሮሚያ ክልል የወጡ ተፈናቃዮችን ወደ ቀደመ ቀያቸው ለመመለስ በክልሎቹ በአመራር ደረጃ እስከ ወረዳ የዘለቀ ውይይት መደረጉን አመልክተዋል።

ተፈናቃዮችን ያለምንም ስጋት መመለስ እንዲቻል የፀጥታ መዋቅሩ ሰላም የማስከበር ስራውን በትኩረት እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ሰላም መስፈኑ በተረጋገጠባቸው አካባቢዎች ተፈናቃዮችን መመለስ መጀመሩንም አቶ አገኘሁ አስታውቀው፣ ቀሪዎቹን በአስቸኳይ ወደ ቀደመ ቀያቸው በመመለስ የመኽር ወቅት ሳያልፋቸው የግብርና ስራቸውን አንዲያከናውኑ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

”ከዚህ በፊት ሰርቶ ሌሎችን መደገፍና መርዳት የለመደ ህዝብ ተረጂ መሆን አይፈልግም” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀደመ ቀያቸው ተመልሰው ለመኖር የስነ ልቦና ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ችግሩ የተከሰተው በህዝብ ለህዝብ ግጭት ለማስመሰል የሚሰሩ የሴራ ፖለቲከኞች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ነገር ግን ቀድሞ የነበረው በመተሳሰብና በመተጋገዝ ላይ የተመሰረተ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አሁንም መኖሩን አስታውቀዋል።

ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ በባለቤትነት እንዲንቀሳቀስም ርዕሰ መስተዳድሩ  ጥሪ አቅርበዋል።

“ተፈናቃዮች ሁኔታዎች ተመቻችተው ወደ ቀደመ ቀያቸው እስኪመለሱ ድረስ መንግስት የእለት ምግብና መሰል ቁሳቁሶችን ከህዝብ ጋር በመተባበር ያቀርባል” ሲሉም  አስታውቀዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መካላከል ምግብ ዋስትና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ተጠሪ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መሳይ ማሩ በበኩላቸው ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በዞኑ የሚኖሩ ተፈናቃዮች ቁጥር ከ21 ሺህ በላይ መድረሱን ተናግረዋል።

መንግስት ህብረተሰቡን፣ ባለሃብቱንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የእለት ደራሽ ምግብና አልባሳት እያቀረበ እንደሚገኝም ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኩታ በር መጠለያ ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል አቶ ሞዴል ሲሳይ “ፖለቲከኞች በፈጠሩት ሴራ የሞቀ ሃብት አፍርተን ቤተሰቦቻችን ከምናስተዳድርበት አካባቢ ተፈናቅለን ተረጂ መሆናችን አሳዝኖናል” ብለዋል።

“መንግስት በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም የሚያሰፍንና ተገቢውን ጥበቃ የሚያደርግ ከሆነ ወደ ቀደመ ቀያችን ተመልሰን  የግብርና ስራችንን ለማስቀጠል ዝግጁ ነን” ብለዋል። በጉብኝቱ የክልልና የዞን አመራሮች ተሳትፈዋል።