ታላቅነት ትልቅነትን ይፈጥራል እንጂ፣ ትልቅነት ታላቅነት አይፈጥርም – ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ

                                                              ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

ሰኔ 04/2013 (ዋልታ) – ታላቅነት ትልቅነትን ይፈጥራል እንጂ ትልቅነት ታላቅነት አይፈጥርም፤ ግሪክና ሮም ዓለምን የቀረጹት በትልቅነታችው ሳይሆን በታላቅነታቸው መሆኑን መርሳት የለብንም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አሳሰቡ፡፡

በእንግሊዝ ግዛት ፀሐይ አትጠልቅም የተባለው እንግሊዝ ትልቅ ሆና ሳይሆን በጊዜው ታላላቅ እንግሊዛውያን በአንድም በሌላም መንገድ በፈጠሩት የታላቅነት ማንነት መሆኑንም ገልጸዋል።

ስፔንና ኦቶማን ቱርክ በአንድ ወቅት ዓለምን ያንቀጠቀጡት በትልቅነት አይደለም፤ስለዚህ ትልቅነት ሊያመጻድቀን ትንሽነትም ሊያሸማቅቀን አይገባም ነው ያሉት።

ጥረታችን በታላላቅ ኢትዮጵያውያን በኩል የኢትዮጵያን ታላቅነት መፍጠር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታላቅነታችንን የምንፈጥረው ደግሞ በታላላቅ ሐሳቦች የታነጹ ታላላቅ ዜጎችንና መሪዎችን በመፍጠር ነው ብለዋል።

ታላቅ ሀገር የሚኖረን ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ ታላላቅና ጽኑ ተቋማትንና ድንበር ዘለል ዓለም አቀፍ አስተሳሰብና ባህልን መፍጠር ሲቻል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ታላቅነት የሚፈጠረው በመደመር፣ በአንድነትና በወንድማማችነት ላይ ተመሥርቶ ታላላቅ ሥራዎችን በጋራ መሥራት ሲቻል መሆኑን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡