ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ናኦሚ ግርማ የ2020 የአሜሪካ ምርጥ ወጣት ተጫዋች ሆና ተመረጠች

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ናኦሚ ግርማ

የአሜሪካ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አምበል የሆነችው ናኦሚ ግርማ የ2020 የአሜሪካ ምርጥ ወጣት ተጫዋች ሆና ተመርጣለች።

በዚህ ዓመት ለዋናው ብሔራዊ ቡድን መመረጥ የቻለችው የተከላካይ መስመር ተጫዋቿ በ2019 የኮሌጅ ቡድኗ ስታንፎርድ ዋንጫ እንዲያነሳ የረዳች ሲሆን የ PAC-12 ምርጥ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ተብላ ተመርጣም ነበር።

ከ20 ዓመት ብሔራዊ ቡድኑ በሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ እና ካሪቢያን ሃገራት ዋንጫ (ኮንካካፍ) ውድድር ቡድኑን በአምልነት እየመራች በስድስት ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ አንድ ጎል ብቻ እንዲያስተናግድ ከመርዳቷ ባሻገር በኮሮና ምክንያት በተሰረዘው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ውድድር እንዲያልፍ እና ሜክሲኮን 4 ለ 1 አሸንፎ የውድድሩን ዋንጫ እንዲያነሳ ትልቅ ሚና መጫወቷን ሶኮር ኢትዮጵያ ዘግቧል።

ይህን ተከትሎም ናኦሚ የአሜሪካ ምርጥ ወጣት ተጫዋች ተብላ ለመመረጥ በቅታለች ያለው የሶከር ኢትዮጵያ ዘገባ በ23 ዓመት የሽልማቱ ታሪክም ሁለተኛዋ የተከላካይ ተጫዋች ሆናለች።

በ1980ዎቹ ወደ አሜሪካ ካቀኑት ወላጆቿ ግርማ አወቀ እና ሰብለ ደምሴ በአሜሪካ 2000 ላይ ለተወለደችው የ20 ዓመቷ ወጣት ናኦሚ ”አስገራሚ ዓመት ነበር ብሏል ዘገባው።

አሜሪካን መወከል ትልቅ ክብር ነው፣ ምንም እንኳ የዓለም ዋንጫው ቢሰረዝም ቡድናችን ባሳካው ስኬት ሁሉ ትልቅ ኩራት ተሰምቶኛል ብላለች።

ዓመቱ በታሰበው መልኩ መጓዝ ባይችልም ለአሰልጣኞቼ እና የህክምና ክፍሉ መጫወት እንድንቀጥል ስላደረጉ አመሰግናለሁ ብላለች ናኦሚ ግርማ ።

ካለፉ የውድድሩ አሸናፊዎች ተርታ መሰለፍ እጅግ አስደሳች ነው፣ ለዚህም ቤተሰቦቼ፤ በተለይ ወንድሜ ሲያግዘኝ ነበር፣ የስታንፎርድ እና የብሔራዊ ቡድን ቤተሰቦቼንም እንደ ተጫዋች እና እንደ ግለሰብ ላበረከቱልኝ መልካም ነገሮች በሙሉ አመሰግናለሁ።” ስትል ከሽልማቱ በኋላ ለዩኤስ ሶከር አስተያየቷን ሰጥታለች።

የአሜሪካ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ላውራ ሀርቬይ ናኦሚን” ምርጥ ግለሰብ እና መሪ” ሲሉ አሞካሽተው “በቡድን ጓደኞቿ የተከበረች እና ቡድኑን ከፊት የምታስቀምጥ አይነት ተጫዋች ናት ብለዋል በአስተያየታቸው።

በዚህ ሽልማት ምርጫ ላይ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች፣ በ2020 ለብሔራዊ ቡድን የተጠሩ ተጫዋቾች፣ የእግር ኳስ ማኅበሩ ቦርድ ዳይሬክተሮች፣ የሴቶች ሊግ፣ የሜጀር ሊግ ሶከር እና የመሳሰሉ የሀገሪቱ የእግር ኳስ አካላት የሚሳተፉ ሲሆን ይህ ሽልማት በ1998 ሲጀመር የመጀመሪያው አሸናፊ የነበሩት የወቅቱ የአሜሪካ ሶከር (የሀገሪቱ እግርኳስ ማኅበር) ፕሬዚዳንት ሲንዲ ፓርሎው ናቸው።