ቶተንሃም አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆን አሰናበተ

አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ

ሚያዝያ 11/2013 (ዋልታ) – ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከ17 ወራት በኋላ አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆን ማሰናበቱን አስታወቀ።

ጆዜ ሞሪንሆ ከማንቸስተር ዩናይትድ ከተሰናበቱ በኋላ በለንደኑ ክለብ አንድ ዓመት ከአምስት ወራት ቆይተዋል።

ፖርቹጋላዊው ሞሪንሆ ቶተንሀምን ለማሰልጠን የተስማሙት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2019 ላይ ማውሪሲዮ ፖቸቲኖን ተክተው ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ቶተንሀም በሞሪንሆ እየተመራ ስድስተኛ ሆኖ ነበር የጨረሰው።

አሁን ቶተንሀም በፕሪምየር ሊጉ ሰባተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በማንቸስተር ዩናይትድ ሶስት ለአንድ ተሸንፎ ከኤቨርተን ደግሞ ሁለት አቻ ተለያይቷል። በተጨማሪም ባለፈው ወር ከአውሮፓ ሊግ በስላቪያ ፕራግ ተሸንፈው ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል።

የሆዜ ሞሪንሆ ረዳት አሰልጣኞች ጃዎ ሳክሪሜንቶ፣ ኑኖ ሳንቶስ፣ ካርሎስ ላሊን እና ጊዮቫኒ ሴራ አብረው መባረራቸውም ተገልጿል።

የቶተንሀም ኃላፊ ደንኤል ሌቪ ”ሞሪንሆ እና ረዳቶቻቸው ቡድናችን ከባድ ጊዜያትን ሲያሳልፍ አብረውን ነበሩ” ብለዋል። ”ሞሪንሆ እውነተኛ ፕሮፌሽናል አሰልጣኝ ናቸው። በዚህ በወረርሽኙ ወቅት እንኳን ብዙ ነገሮችን ተቋቁመዋል” ሲሉም አክለዋል፡፡

”በግል ደረጃ ከሞሪንሆ ጋር መስራት በጣም ያስደስተኛል፤ ሁለታችንም ባሰብነው መልኩ ነገሮች ባለመሳካታቸውና ይህ በመፈጠሩ አዝኛለሁ’፤ “ሁሌም ቢሆን ለሞሪንሆ በራችን ክፍት ነው፤ በዚህ አጋጣሚ አሰልጣኙ እና ረዳቶቻቸው ላደረጉት ነገር በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡

በዚህ የውድድር ዓመት ሆዜ ሞሪንሆ በአሰልጣኝነት ታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ቶተንሀምን ይዘው 10 ጊዜ ሽንፈት አስተናግደዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የትኛውም የፕሪምየር ሊጉ ቡድን በያዝነው የውድድር ዓመት እንደ ቶተንሀም ቀድመው ግብ አግብተው ሽንፈት አላስተናገዱም። ቶተንሃሞች ቀድመው ግብ ማስቆጠር ጀምረው እስካሁን 20 ነጥቦችን ጥለዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።