ኒስክ ካፒታል የኢንቨስትመንት ባንክ በኢትዮጵያ መሰማራት እንደሚፈልግ ገለጸ

 

መቀመጫውን ዋሽንግተን ያደረገው ኒስክ ካፒታል የኢንቨስትመንት ባንክ በኢትዮጵያ መሰማራት እንደሚፈልግ ገለጸ፡፡

በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም ከተቋሙ የምስራቅ አፍሪካ ቢሮ ኃላፊ ኢሬኔ ዱኩምዌናዮ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው ኒስክ ካፒታል የኢንቨስትመንት ባንክ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በሚሰራበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

በውይይቱ አምባሳደር መለስ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተወሰደ ካለው ፈጣን የኢኮኖሚ ማሻሻያ አንፃር ኒስክ ካፒታል በኢንቨስትመንት ለመሰማራት እድሉ እንዳለው ገልጸዋል።

ኢሬኔ ዱኩምዌናዮም የፋይናንስ ተቋሙ በኢትዮጵያ ለመስራት የሚያስችል ሰፊ የፋይናንስ አቅም እንዳለው መግለፃቸውን ከኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ባንኩ ኬንያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ የተለያዩ ሃገራት ጽህፈት ቤቱን ከፍቶ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡