ናሳ ምርምር ለማድረግ ሁለት ልዑኮችን ወደ ቬኑስ እንደሚልክ ገለጸ

ግንቦት 26/2013 (ዋልታ) – ናሳ የስነ ምድርና የከባቢ አየር ምርምር ለማድረግ ሁለት ልዑኮችን ወደ ቬኑስ እንደሚልክ አስታወቀ፡፡

እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ2028 እና 2030 ወደ ቬኑስ ለሚደረጉት ተልዕኮዎች እያንዳንዳቸው 500 ሚሊየን ዶላር እንደሚወጣባቸውም ተገልጿል።

የናሳ አስተዳዳሪ ቢል ኔልሰን ተልዕኮዎቹ “ከ30 ዓመታት በላይ ያልደረስንበትን ፕላኔት ለመመርመር እድል ይሰጡናል” ብለዋል፡፡

በፕላኔቷ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ምርምር የተደረገው እንደ አውሮፓውያኑ 1990 ነበር።

ናሳ ተልዕኮዎቹን ለመፈጸም ከውሳኔ ላይ የደረሰው የተለያዩ ግምገማዎችን ካከናወነ፣ ያላቸውን ሳይንሳዊ አስፈላጊነትና አዋጭነት ካረጋገጠ በኋላ ነው ተብሏል፡፡

ሁለት ጥምር ተልእኮዎች ቬኑስ እንዴት እርሳስ [lead] ማቅለጥ የሚችል የእሳትን ገጽታ የተላበሰ ዓለም ሊሆን እንደቻለ ለመረዳት ዓላማ ያደረጉ መሆናቸውን አስተዳዳሪው ኔልሰን አስረድተዋል፡፡

ቬኑስ ከጸሀይ በመቀጠል ሁለተኛዋ ሞቃታማ ፕላኔት ስትሆን፣ እስከ 500 ሴልሺየስ የምትሞቅና እራሳስን ማቅለጥ የሚችል የአየር ሁኔታ ላይ የምትገኝ መሆኗን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡