ኔልሰን ማንዴላ ቀን

ደቡብ አፍሪካን ከጨቋኝና ዘረኛ የአፓርታድ ስርዓት ነጻ ለማውጣት ያደረጉት አስተማሪ ትግል ኔልሰን ማንዴላ (ማዲባ ) ለጥቁር ሕዝቦች እንዲሁም በጭቆና ውስጥ ላሉ የዓለም ሕዝቦች የነጻነት ምልክትና የትግል ፋና በመሆን የማይጠፋ ደማቅ ታሪክ የጻፈ ነው።

የቀድሞው ደቡብ አፍሪካ የነጻነት ታጋይ እና የሀገሪቱ መሪ የነበሩት ኔልሰን ማንዴላ የተወለዱት 1918 ሐምሌ 18 ነው። ቀኑ በየዓመቱ በስማቸው እንዲከበር የተባበሩት መንግስታት ውሳኔ ያስተላለፈው እ.ኤ.አ ጥቅምት 2009 ነበር፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከዚህ ሐሳብ ላይ የደረሰው ታላቁ የነጻነት ታጋይ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ጥለውት ያለፉትን ሌጋሲ ለማጉላትና ለማስታወስ በማሰብ መሆኑ ይነገራል።

ማዲባ እኩልነትን፣ የሰው ልጆች ክብርን፣ በማስመልከት በሁሉም መስመሮችና ቡድኖች ጋር ውይይትና አጋርነትን ማከናወን የሚሉት ቁልፍ መርሆቻቸው እንደነበረ ይገለጻል፡፡

ኔልሰን ማንዴላ ታላቅ መሪ፣ ቆራጥ የእኩልነት መብት አራማጅ እና የደቡብ አፍሪካ የሰላም አባት በመባል ይታወቃሉ።

በልደት ቀናቸው የተሰየመው የማንዴላ ቀን በየዓመቱ በተለያዩ መሪ ቃሎች የሚከበር ሲሆን በያዝነው ዓመት “ድህነትንና የሀብት ልዩነትን መታገል አሁንም በእጃችን ላይ ነው” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው።

ማዲባ የህጻናት እድገትና በምግብ ራስን መቻል ላይ ትኩረት ያደረገ ማኀበራዊ ፍትህ ግድ የሚላቸው መሪ ስለነበሩ መሪ ቃሉ ተመርጧል።

የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ የማንዴላ ቀንን አስመልክቶ “ኔልሰን ማንዴላ አንድ ሰው የተሻለች ዓለም በመገንባት ረገድ ሊያመጣ የሚችለውን ልዩነት አሳይቶናል” ሲሉም ገልጾአቸዋል።

ማዲባ በዘረኛው የአፓርታድ ስርዓት የ27 ዓመታት እስር ነጻ ከወጡ በኋላ ደቡብ አፍሪካን እ.ኤ.አ ከ1994-1997 በፕሬዝዳንትነት መርተዋል።

የነጻነት ትግል ቀንዲል እና ለመብት ተሞጋቾች ምሳሌ ያተረፉ ኔልሰን ማንዴላ በፈረንጆቹ ታህሳስ 5 ቀን 2013 ከዚህ ዓመት በሞት ተለይተዋል።