አለም ባንክ ኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ መደገፋን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አመራሮች በኢትዮጵያ የአለም ባንክ ዳይሬክተር  በዶክተር ኦስማን ዲዮን ከተመራው የአለም ባንክ የሉኡካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚንስትር አብርሃም በላይ (ፒ ኤች ዲ) አለም ባንክ በተለያዩ ዘርፎች በኢትዮጵያ  በተለይም የዲጂታል ፋውንዴሽን ስራ እና በሚኒስቴር መስርያ ቤቱ የሚከናወኑ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ያሳየውን ፍላጎትና ድጋፍ አድንቀዋል።

ሚኒስትሩ የቴሌኮም ዘርፉን ፕራይቬታይዝ የማድረግ ስራ ላይ ከፖሊሲ አንጻር የነበሩ ስራዎች ከአለም ባንክ ጋር በቅርበት መስራታቸውን አስታውሰዋል።

በውይይቱ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን ሙሀመድ (ፒ ኤች ዲ) በዲጂታል 2025 ፕሮግራም ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች የዲጂታል አሰራርን ለመዘርጋት የሄደችውን ርቀት ለሉዕካን ቡድኑ አብራርተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮግራሙ ወደ ትግበራ ለመግባት ከልዩ ልዩ አካላት ጋር ድጋፍና ትብብር በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተቀናጅቶ ለመስራት  የልየታ ስራ ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የአለም ባንክ ተወካዩ አለም ባንክ በኢትዮጵያ የሚያደርጋቸውን ድጋፎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው በተለያዩ ሀገራት ካገኟቸው ተሞክሮዎች አንጻር የዲጂታል አጀንዳን ትግብራ ለማረጋገጥ የተሻለ ጅምር እንዳለ ተናግረዋል።

በተለይም ቬትናም የአለም ባንክ ፕሮግራም በሚመሩበት ወቅት ካላቸው ልምድ አንጻር በኢትዮጵያ ያለው ጅምር ተስፋ ሰጭ ነው ብለዋል።

አለም ባንክ ግብርና፣ ቱሪዝም፣ ከተማና ትራንስፖርት እንዲሁም ሌሎች ዘርፎች በቴክኖሎጂና ዲጂታይዜሽን ለማዘመን በኢትዮጵያ የሚደረገውን ጥረት ከመንግስት ጎን በመሆን እንደሚደግፍ ቃል ገብተዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር  የጀመራቸውን የተለያዩ ፕሮግራሞች ውጤታማ ለማድረግ የአለም ባንክ የቴክኖሎጂ አማካሪዎች ቡድን ለመመደብ ዝግጁ ነን ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳሬክተር ዶክተር ኦስማን ዲዮን በበርካታ ሀገራት የአለም ባንክ ፕሮግራሞችን የመሩ ሲሆን በአሁኑ ስአት መቀመጫቸውን ኢትዮጵያ ላይ አድርገው የሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ የአለም ባንክ ፕሮግራሞች ይመራሉ።