አሜሪካ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባቶችን ድጋፍ ልታደርግ ነው

ሰኔ 3/2013(ዋልታ) – አሜሪካ እ.ኤ.አ በተያዘው እና በቀጣዩ ዓመት ተግባራዊ የሚሆን 500 ሚሊየን ብልቃጥ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት አንድ መቶ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት እንደምትሰጥ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ተናግረዋል፡፡

አሜሪካ ይህን ያህል መጠን ያለው ክትባት ድጋፍ ማድረግ የሚያስችላትን የክትባት አቅርቦት ለማግኘትም በሀገሪቱ ካሉ የክትባት አምራች ድርጅቶች ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ፕሬዚደንቱ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

አሜሪካ በዚህ ዓመት 200 ሚሊየን ብልቃጥ እንዲሁም እስከ ቀጣይ ዓመት አጋማሽ ድረስ ለምታቀርበው የ300 ሚሊየን ብልቃጥ ክትባት ለፋይዘር እና ባዮቴክ ለተባሉ የክትባት አምራች ድርጅቶች ትርፍን ታሳቢ ያላደረገ ክፍያ እንደምትፈጽም አልጀዚራ ኒውዮርክ ታይምስን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

ፕሬዚደንቱ ይህን የተናገሩት በአውሮፓ ሊያደርጉት ካሰቡት ጉብኝት ቀደም ብሎ አሜሪካ ክትባቱን በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ተደራሽ ማድረግ ላይ ችግር እንዳለባት በመገለጹ እና ፕሬዚደንቱም ጫና ውስጥ በመግባታቸው ምክንያት መሆኑም ተዘግቧል፡፡

ይህ የክትባት ድጋፍ ዛሬ በእንግሊዝ በሚጀመረው የቡድን 7 አባል ሀገራት በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ይፋ እንደሚያደርጉትና ድጋፉም ለ92 ዝቅትኛ ኢኮኖሚ ላላቸው ሀገራትና ለአፍሪካ ህብረት እንደሚሰጥ ነው የተገለጸው፡፡

ዛሬ በሚጀመረው የቡድን 7 አባል ሀገራ ስብሰባ ላይ በደሃ እና በኢንደስትሪ በበለጸጉ ሀገራት መካከል የሚታየውን የኮሮና ቫይረስ ክትባት ስርጭት ኢ-ፍትሃዊነት እንዴት ማስተካከል እንደሚቻል በቀዳሚ አጀንዳነት ይዞ እንደሚወያይበት ተገልጿል፡፡

ባለፈው ሳምንት አሜሪካ 80 ሚሊየን ብልቃጥ ክትባቶችን በዓለም ጤና ድርጅት በኩል ክትባቶችን በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ተደራሽ ለሚያደርገው የኮቫክስ ፕሮግራም መለገሷ  በዘገባው ተመላክቷል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በክትባቱ ስርጭት ላይ የሚታየውን ኢ-ፍትሃዊነት ለማስተካከል እና የዓለምን ህዝብ ለመከተብ በትንሹ 11 ቢሊየን ብልቃጥ ክትባት እንደሚያስፈልግ ይፋ አድርጓል፡፡