አሜሪካ በሩስያ የነዳጅ ማስተላለፊያ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ አነሳች

ግንቦት 12/2013 (ዋልታ) – የባይደን አስተዳደር በሩስያና በጀርመን መካከል አወዛጋቢውን የነዳጅ ማስተላለፊያ እየገነባ በሚገኘው ኩባንያ ላይ ተጥሎ የነበረውን ማዕቀብ አነሳ።

በተጨማሪም ኖርድ ስትሪም ፕሮጀክት 2 እየተባለ የሚጠራውን ይህንን ግንባታ እየመራ የሚገኘውንና የቭላድሚር ፑቲን አጋር እንደሆነ በሚነገርለት ተቋም አመራር ላይ የተጣላውን ማዕቀብም አሜሪካ አንስታለች።

የባይደን አስተዳደር ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ጉዳዩን ለኮንግረንስ ካቀረበ በኋላ ነው ተብሏል።

ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሩ ለሞስኮ ታላቅ የፖለቲካ ድል ነው።

በባልቲክ ባህር በኩል ነዳጅ ከሩሲያ ወደ ጀርመን የሚጓጓዝበት መስመር ግንባታ 95 በመቶ ተጠናቋል።

የማዕቀቡን መነሳት በሚያትተው የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት መግለጫ ላይ የነዳጅ መስመሩን ሲገነባ በቆየው ተቋምና ዋና ሥራ አስጻሚው ላይ የተጣለው ማዕቀብ ለአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም ሲባል መነሳቱን ይገልጻል።

አሜሪካ በግንባታው ላይ እየተሳተፉ ባሉ አራት መርከቦች ላይም ማዕቀብ ጥላ የነበረ ቢሆንም ይህ የግንባታ ሂደቱን ለመግታት በቂ እንዳልሆነ ሲገለጽ ነበር።

ውሳኔውን ተከትሎ የሩሲያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቨሮቭ አሜሪካና ሩሲያ “የከረረ ልዩነት” ቢኖራቸውም የጋራ ጥቅማቸው በሚገናኙበት ቦታ በጋራ መሥራት አለባቸው ብለዋል።

የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው፣ “ባይደን ከሩስያ ጋር የተረጋጋ ግንኙነት መመስረት ይፈለጋሉ” ብለዋል።

የ11 ቢሊየን ዶላር ግንባታ እንደሆነ የተነገረለትን የኖርዲክ ስትሪም ግንባታ ፕሮጀክት 2 በተመለከተ የባይደን አስተዳደር ያሳለፈውን ማዕቀብ የማንሳት ውሳኔ የተቃወሙ ግለሰቦች እንዳሉና አንዳንዶቹ የፕሬዝዳንቱ ፓርቲ አባላት መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።