አሜሪካ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ በሆኑ አጀንዳዎች ከአፍሪካ ጋር በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ ናት- ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

አሜሪካ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ በሆኑ አጀንዳዎች ከአፍሪካ ጋር በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗን አዲሱ የአገሪቷ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቱ ነገና ከነገ በስትያ የሚካሄደውን 34ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ስብሰባ አስመልክተው በበይነ መረብ የቪዲዮ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ፕሬዚዳንት ባይደን በመልዕክታቸው ያለፈው የፈረንጆች ዓመት ዓለም ምን ያህል እርስ በእርስ እንደተሳሰረችና አንድ መሆኗን ለመመልከት ችያለሁ ብለዋል።

የዓለም ሕዝቦች ዕጣ ፈንታም እርስ በእርሱ የተሰናሰነ መሆኑን መገንዘባቸውን የገለጹት ፕሬዝዳንት ባይደን፣ በዚህም የተነሳ እርሳቸው የሚመሩት የአሜሪካ አስተዳደር ከዓለም አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ከነዚህም ዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል የአፍሪካ ኅብረት አንዱ መሆኑን በመጠቆም፣ አስተዳደራቸው ከኅብረቱ ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠናክር አምልክተዋል።

በዚህም የጋራ የሆነውን ራዕይ በማሳካት መጪውን ጊዜ የተሻለ ማደረግ እንደሚቻል ተናግረው፣ በመጪው ጊዜ ለንግድና ኢንቨስትመንት ትኩረት በመስጠት የጋራ ብልጽግናን እውን ማድረግ እንደሚቻል ፕሬዝዳንቱ መግለፃቸውን ቢቢሲ አስነብቧል፡፡