አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ከጅቡቲው የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጋር ተወያዩ

በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ከጅቡቲው የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ዘካሪያ ሼክ ኢብራሂም ጋር በሁለቱ ሀገራት ግንኙነትና አካባቢያዊ የፀጥታ ጉዳየች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ በመከላከያ ሰራዊት የተደረገውን ገድል ከግምት ውስጥ በማስገበት በጅቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኤል ኡመር ጌሌ የተፈቀደውን ከፍተኛ የወታደራዊ ኒሻን ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ መሸለማቸው የኢትዮጵያን መንግስት፣ የመከላከያ ሰራዊቱንና መላው ኢትዮጵያዊያንን ያስደሰተና ጅቡቲ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ሥፍራ የሚያመላክት  መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተላከውን ከፍተኛ ምስጋና ለጄኔራሉ አቅርበውላቸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ጁንታው የህወሃት ቡድን በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት በአካባቢው ህግና ሥርዓትን ለማስከበር ያደረገውን እንቅስቃሴ ተከትሎ የጅቡቲ መንግስትና ህዝብ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ድጋፍ ቀድመው ያረጋገጡ መሆኑን  ያስታወሱት  አምባሳደር ብርሃኑ ጅቡቲ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ መሆኗን ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል።

የጅቡቲ ጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ዘካሪያ በበኩላቸው የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት ታሪካዊና ህዝብ ለህዝብ የተሳሰረ መሆኑን ገልፀዋል።

በመከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የተመራው ቡድን በጅቡቲ በነበረው ቆይታ በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው ግንኙነትና በመከላከያ ኃይሎችም መካከል ተባብሮ መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ለቀረበላቸው ምስጋና የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው ኢትዮጵያ ስትራቴጂክ አጋራችን ናት ያሉት ጄኔራል ዘካሪያ ግንኝነቱን ይበልጥ ለማጠናከር በጅቡቲ በኩል ያለውን ቁርጠኝነትም በድጋሚ ማረጋገጣቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ሁለቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከሁለትዮሽ ጉዳዮች በተጨማሪ በአካባቢያዊ የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን በሀገራቱ ብሎም በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍን ተብብረው መሥራት እንደሚገባቸውም በውይይታቸው ወቅት አንስተዋል፡፡