አምብሮ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድኖች ትጥቅ ማቅረብ የሚያስችለውን ስምምነት አራዘመ

መጋቢት 24/2013 (ዋልታ) – አምብሮ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ለኢትዮጵያ የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድኖች ትጥቅ ለማቅረብ የሚስችለውን ስምምነት ለአራት ዓመታት አራዘመ።

አምብሮ ከፈረንጆቹ 2019 ጀምሮ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ይፋዊ የቴክኒካል ስፖንሰር በመሆን ሲሰራ ቆይቷል።

በአዲሱ ስምምነት መሰረትም አምብሮ ኩባንያ ለወንዶች ፣ ሴቶች ፣ ወጣቶች እና ለታዳጊ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድኖች ሙሉ የጨዋታ ትጥቆች፣ የመለማመጃ አልባሳት እና ከሜዳ ውጭ የሚለበሱ አልባሳትን የሚያቀርብ ይሆናል።

የቴክኒክ እና የአስተዳደር አባላትም በአምብሮ ትጥቅ አምራች የተዘጋጁ አልባሳትን እንደሚለብሱ በስምምነቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ አምብሮ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲያቀርባቸው ለነበሩ ጥራት ያላቸው ምርቶች ምስጋና አቅርበዋል።

ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር የተደረሰው ስምምነት አምብሮን ከአፍሪካ ባለፈ ዓለም አቀፍ ተደራሽነቱን የሚያሰፋ መሆኑን በደቡብ አፍሪካ የኩባንያው ሃላፊ ዴቪድ ሪኬትስ መግለፃቸውን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።