አቶ ደመቀ መኮንን ከእንግሊዝ የረሀብ መከላከል እና የሰብዓዊ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ

አቶ ደመቀ መኮንን

ግንቦት 17/2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከእንግሊዝ የረሃብ መከላከልና የሰብዓዊ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ ሚስተር ኒክ ዳየር ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው ወቅትም ሁለቱ ወገኖች ትግራይ ክልልን የተመለከቱ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ በክልሉ ሰብዓዊ ድጋፎች ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እየተደረገ ስለሚገኘው ድጋፍን ጨምሮ በክልሉ ስላለው ሰፊ የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ሥራዎች ለልዩ መልዕክተኛው ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡

በዚህም በመጀመሪያ ዙር 4.5 ሚሊየን እና በሁለተኛ ዙር ደግሞ 2.9 ሚሊየን ሰዎችን ፍላጎት ያገናዘበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች በተሳካ ሁኔታ መከናወናቸውን ገልፀው፣ ሶስተኛው ዙርም በቅርቡ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም መንግስት የተፈናቃይ ወገኖችን ችግሮች ለመቅረፍ እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ተደራሽነትን ለማስፋት እየተደረገ ስላለው ጥረትም ገለጻ አድርገዋል፡፡

በክልሉ ተፈጽመዋል የተባሉ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ የተለያዩ አካላት የጋራ ምርመራ ለማድረግ የሚያስችል አበረታች እርምጃዎችን እየወሰዱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢፌዲሪ ጠቅላይ አቃቢ ህግና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም መሰል ምርመራ በማካሄድ ተሳታፊ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።

ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማህበራት፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሌሎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይቶችን በማካሄድ ክልሉን ወደ መደበኛ ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ አገራት መካከል የቆየውን ዘመን ተሻጋሪ ግንኙነት በማውሳት፣ ግንኙነቱን የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው መወያየታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡