አቶ ደመቀ መኮንን ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ

ግንቦት 12/2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር እና ለአፍሪካ ህብረትና ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ተጠሪ ከሆኑት ሃሚድ ኑሩ ጋር ተወያዩ።
አቶ ደመቀ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ በተከሰቱ ሰው ሰራሽ ግጭቶች እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት ግንባር ቀደም በመሆን እያበረከተ ስላለው ከፍተኛ ድጋፍ አመስግነዋል።
አያይዘውም ድርጅቱ የ2020 የዓለም የሰላም የኖቬል ሽልማት አሸናፊ በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በሆነችበት ወቅት ድርጅቱ የሰብዓዊ እርዳታ በማድረግ የተጫወተውን ሚና አንስተው፣ ለዚህም የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዴቪድ ቫሲሊን አድንቀዋል።
ሚስተር ሃሚድ ኑሩ በበኩላቸው፣ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ አግባብነት ካላቸው ተቋማት ጋር የቅርብ ትብብር እየተደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
በአፍሪካ አገር በቀል የትምህርት ቤቶች ምገባ ፕሮግራም ማዕቀፍ በኢትዮጵያ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ተግባራዊ በተደረጉ ፕሮግራሞች አበረታች ውጤቶችን መመዝገባቸውንም አንስተዋል።
በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እስከ ሁለተኛ ዙር ተደራሽ መደረጉንና እና በቅርቡም ሶስተኛ ዙር አቅርቦት ተግባራዊ እንደሚሆን አንስተው፣ ለዚህም ድርጅቱ የሚኖረው ሚና ጉልህ እንደሚሆን ያላቸውን አምነት አቶ ደመቀ ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል ሰላም ማስፈን፣ መልሶ ማቋቋም እንዲሁም ሁሉን አካታች የሆነ ውይይት ለማካሄድ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው፣ ካለው የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት አንጻር ክፍተቶች በመኖራቸው የዓለም አቀፉ ማህበረሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደረግ ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል።