አቶ ደመቀ ከአውሮፓ ኅብረቱ ልዩ መልእክተኛ ፔካ ሀቬስቶ ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ

የአውሮፓ ኅብረት ልዩ መልእክተኛ

ሚያዚያ 1 /2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአውሮፓ ኅብረት ልዩ መልእክተኛ እና የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሀቬስቶ ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ።

በውይይታቸውም ትግራይ ክልል የሚሰያስፈልገውን ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በተመለከተ አቶ ደመቀ መኮንን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በክልሉ ተፈፅሟል ስለሚባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ምርመራ ከማደረግ አንጻር የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቀደም ሲል በማይካድራ እንዲሁም በመቀጠልም በአክሱም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ምርመራ በማድረግ ያቀረበውን ሪፖርት አስታውሰው፣ በመንግሥት በኩል በገለልተኛ አካላት አማካይነት ምርመራ እንዲደረግ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሳተፉ አካላትን ለህግ ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነትንም አረጋግጠዋል።
ሚስተር ፔካ ሀቪስቶ በበኩላቸው ከሁለት ወራት በፊት በአገራችን ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ ከዚያ በኋላ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ተደራሽነትና የሚዲያ አካላት በክልሉ በመገኘት እንዲዘግቡ ከማድረግ አንጻር በመንግሥት የተከናወኑ ተግባራት በአዎንታዊነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ ያደረጉት ጉብኝትም ይህንን የሚያረጋግጥ መሆኑን አንስተዋል። ግጭት ያለባቸው የተወሰኑ አካባቢዎች እርዳታ የሚያስፈለጋቸው ዜጎች ተገቢው እርዳታ እንዲደርሳቸው ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
አያይዘውም የአውሮፓ ኅብረት የሰብዓዊ እርዳታ ኤጀንሲዎች በክልሉ ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለተደራሽ አካላት ተገቢው ድጋፍ ማቅረብ እንዲቻል የፍላጎት አጠቃላይ ዳሰሳ ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ አንዲሚወጣ መገለጹንም በአዎንታዊነት እንደሚገነዘቡት ገልጸው፣ ሂደቱ እንዲፋጠን ጠይቀዋል።
በትግራይ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀድሞ ቦታቸው ለመመለስ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግም ነው ሚስተር ፔካ ሀቪስቶ የገለጹት።
በመንግሥት በኩል በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ከመጪው የዝናብ ወቅት በፊት ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም አንዲቻል ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን አቶ ደመቀ ገልጸዋል።
የታላቁ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተም ኢትዮጵያ በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ድርድሩ በውጤት አንዲጠናቀቅ ላደረጉት ጥረት ከበሬታ ያላት መሆኑን አቶ ደመቀ ገልጸዋል።
በቀጣይም በአፍሪካ ሕብረት አመቻችነት የሶስትዮሽ ድርድሩ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸውላቸዋል።
ሚስተር ሀቬስቶ በበኩላቸው የሕዳሴው ግድብ ድርድር ከመጪው ክረምት ከሚከናወነው የውኃ ሙሌት በፊት ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፣ በአውሮፓ ኅብረት በኩልም የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ፍላጎት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮ-ሱዳንድ የድንበር ውዝግብን ሁለቱ አገራት በድርድር መፍታት ያለባቸው መሆኑን ሚስተር ሀቬስቶ አንስተዋል።
አቶ ደመቀ በበኩላቸው የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሱዳን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መሬት በወረራ መያዟን ተከትሎ ማውገዝ የሚጠበቅበት ቢሆንም ይህንን አለማድረጉ አሳዛኝ መሆኑን ገልጸው፣ በኢትዮጵያ በኩል ችግሩ በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኝ ጽኑ አቋም ያለ መሆኑን ማስረዳታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።