አዲሱ የኮሮናቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ጥንቃቄ እየተደረገ ነው – የጤና ሚኒስቴር

በአንዳንድ ሃገራት እየታየ ያለው አዲስ የኮሮናቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ከመስከረም ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ በእንግሊዝ መከሰቱ ይታወሳል ይኸው ቫይረስ በአጭር ጊዜ ወስጥ አሜሪካና ካናዳም ገብቷል።

በደቡብ አፍሪካና በናይጄሪያም በእንግሊዝ ሃገር ከተገኘው የቫይረሱ ዝርያ የተለየና አዲስ አይነት የኮሮናቫይረስ ዝርያ በቅርቡ ተከስቷል።

የቫይረሱ ዝርያ ከመጀመሪያው ቫይረስ ጋር ሲነጻጸር የህመም ደረጃን የመጨመርም ሆነ ለሞት የማጋለጥ እድሉ ምን ያክል እንደሆነ በጥናት አልተረጋገጠም።

ያም ሆኖ አዳዲሶቹ የቫይረሱ ዝርያዎች በፍጥነት ከሰው ወደ ሰው የመዛመትና የመተላለፍ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።

አሁን፣ አሁን የሚወጡት ጥናቶችም አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ቀደም ሲል ለቫይረሱ የተሰሩት ክትባቶች እንደሚከላከለው አመላክተዋል።

ይሁን እንጂ እነዚህ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች በፍጥነት ስለሚዛመቱ ለኢትዮጵያ ስጋት መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዲኤታዋ ሰሃረላ አብዱላሂ ተናግረዋል።

በተለይም በደቡበ አፍሪካና በናይጄሪያ የተገኙት የቫይረሱ ዝርያዎች ከቅርበት አንጻር ለኢትዮጵያ ስጋት ስለሚሆኑ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።

ይህን ተከትሎም በተለይም ከውጭ ወደ ሃገር ኢትዮጵያ የሚገቡትን መንገደኞች የመመርመር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው ያመላከቱት።

ያም ብቻ ሳይሆን በድንበር አካባቢም ያለው የቁጥጥር ሥራ መጠናከሩን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የትኛውንም አይነት የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ለመከላከል በጤና ባለሙያዎች የቀረቡትን የመከላከያ ሥልቶች ተግባራዊ ማድረግ መፍትሄ መሆኑንም ጠቁመዋል።

እጅን በሳሙና መታጠብ፣ የአፍና የፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል (ማስከ) ማድረግና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ የሚሉትን መርሆዎች ሊከበሩ ይገባልም ነው ያሉት።

በተለይም አዲሱ የኮሮናቫይረስ ወጣቶችን ያጠቃል የሚል ጥናት መኖሩን ጠቁመው ወጣቶች ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በመጭው የጥምቀት በዓል ላይም ኅብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመው ሁሉም ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በተለይም ቫይረሱ በማኅበረሰብ ውስጥ በስፋት ስለተሰራጨ ጥንቃቄው አብሮ ሊጎለብት ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።