አዲሷ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት የወደቦች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርን ከሃላፊነት አገዱ

መጋቢት 20/2013 (ዋልታ) – አዲሷ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን ከመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ በሆነው የወደቦች ባለስልጣን የገንዘብ ምዝበራ መፈጸሙን የሚያሳይ ሪፖርት መቅረቡን ተከትሎ የባለስልጣኑን ዋና ዳይሬክተር ከሃላፊነት አግደዋል።
ይህ ውሳኔ የፕሬዚዳንትነት ስልጣንን ከያዙ በኋላ የመጀመሪያቸው እንደሆነም ተገልጿል።
ፕሬዚዳንት ሳሚያ የወደቦች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዱስዴዲት ካኮኮን ከሃላፊነት ያገዱት እ.አ.አ በ2019/20 የኦዲት ሪፖርት መሰረት መሆኑም ተጠቁሟል።
የወደቦች ባለስልጣን በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የአራት ቢሊዮን የታንዛኒያ ሽልንግ (የ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር) ጉድለት አሳይቷል።
ለጠፋው የህዝብ ሃብትም ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ ትዕዛዝ የሰጡት ፕሬዚዳንቷ፤ ኤይር ታንዛኒያን ጨምሮ በሌሎች የመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወሰድ አመላክተዋል።
የአገሪቱ የኦዲት ተቋም መረጃ እንደሚያሳየው ባለፉት አምስት አመታት በተለያዩ ተቋማት የ60 ቢሊዮን የታንዛኒያ ሽልንግ (36 ሚሊዮን ዶላር) የገንዘብ ምዝበራ መፈጸሙን ቢቢሲ በዘገባው አስነብቧል።