ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ የነዳጅ ስምምነት ተፈራረሙ

ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ የነዳጅ ስምምነት

ሚያዝያ 04/2013 (ዋልታ) – ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ የኡጋንዳን የነዳጅና የጋዝ ኢንዱስትሪ ለማሳደግ ሦስት ወሳኝ ስምምነቶች ላይ ተፈራረሙ።

ስምምነቱ አዲሷ የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት የውጭ አገር ጉብኝት ሲሆን፣ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ድርሻ እና የት እንደሚሆኑ፣ የነዳጅ ማስተላላፊያ መንገዶች እና ግብርን በተመለከተ ነው ተብሏል።

ስምምነቱም ሁለቱ አገራት የነዳጅ ማስተላላፊያዎቹን ለመገንባትና በፍጥነት ለመጠቀም ያስችላል ተብሏል።

ሁለቱ አገራት 1 ሺህ 443 ኪሎሜትር ርዝማኔ ያለው የነዳጅ ማስተላላፊያ ቱቦ ለመገንባት ተስማምተዋል። ነዳጁ ከኡጋንዳ ምዕራባዊ ክፍል አልበርቲን ከሚባል ቦታ የሚመጣ ሲሆን፣ በማስተላላፊያ ቱቦዎቹ በኩል አድርጎም ወደ ታንዛኒያዋ ታንጋ ወደብ ይደርሳል።

3.5 ቢሊየን ዶላር እንደሚፈጅ የተነገረለት ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ በዓለማችን ላይ ከነሙቀቱ የሚጓጉዝ የመጀመሪያው ማስተላለፊያ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። የመጨረሻ ውሳኔ፣ የገንዘብ ጉዳይና ሌሎች ተያያዥ ነጥቦች ላይ የመጨረሻ ስምምነት እንደሚደረግም ይጠበቃል።

ሁለቱ አገራት የመጨረሻ ስምምነት ላይ ከደረሱ ግንባታው በፍጥነት ይጀመራል ተብሏል።

አገራቱ የነዳጅ ማስተላላፊያ ቱቦው ግንባታ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት እንደሚያጠናክር የገለጹ ሲሆን፣ ግንባታው ሲጠናቀቅም እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚያገኙ ተገልጿል።

ነገር ግን የሁለቱ አገራት ስምምነት ከአካባቢ ተቆርቋሪዎች ከፍተኛ ትችትን አስተናግዷል። የአካባቢ ተቆርቋሪዎቹ እንደሚሉት የነዳጅ ማስተላለፊያው ግንባታ በቪክቶሪያ ሐይቅ እና ሰረንጌቲ የዱር እንስሳት ፓርክ ውስጥ ያሉ እንስሳትና እጽዋት ሊጎዳ ይችላል።

ኡጋንዳ የመጀመሪያውን 1.4 ቢሊየን በርሜል ነዳጅ በአውሮፓውያኑ 2025 እንደምታወጣ ይጠበቃል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።