ኢትዮጵያና ኳታር በዓለም አቀፋዊ መድረኮች በትብብር ለመስራት ተስማሙ

ሰኔ 3/2016 (አዲስ ዋልታ) ኢትዮጵያና ኳታር በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች በትብብር ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለጸ።

ዛሬ የኢፌዲሪ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተላከን መልዕክት ለኳታሩ አሚር ሼክ ተሚም ቢን ሀማድ አልታኒ በሌሲኤል ቤተመንግሰት በመገኘት አስረክበዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መልዕክት የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ መልዕክቱን ባስረከቡበት ወቅት በተካሄደ ውይይት በአገራቱ መካከል የቀደመው ግንኙነት የበለጠ ሊሻሻል በሚችልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ትኩረት ተደርጓል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው አጠቃላይ የኢኮኖሚያዊ ሪፎርሞች፣ የለውጡን ሂደቶችና ትሩፋቶች፣ የምጣኔ ሃብት ዕድገትና ሌሎች ጉዳዮችን አንስተው ኳታር በዘርፉ ተሳትፎዋን እንድታሳድግ የገንዘብ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።

ኢሚር ሼክ ተሚም ቢን ሀማድ አልታኒ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ትልቅ እና ቀደምት ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን አንስተው ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት መስፈን ቁልፍ አላት ብለዋል።

ኳታር በዚህ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ቁርጠኛ ናት ሲሉም ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ከኳታሩ አቻቸው አሊ ቢን አህመድ አል ኩዋሪ ጋር በሁለቱ ሀገራት በፋይናንስ፣ በልማት ትብብር እና በኢንቨስትመንት ትብብር ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።

በውይይታቸው ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ለኳታሩ አቻቸው፣ ለኳታር ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በተቋም ለተቋም ግንኙነትም በትብብር ለመስራት ከስምምነት ደርሰዋል።