ኢትዮጵያን ለማዳን ሁሉም አንድ መሆን ይገባዋል- ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ

ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ

ሚያዝያ 26/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው የተነሱባት አገር በመሆኗ ኢትዮጵያን ለማዳን ሁሉም አንድ መሆን እንደሚገባ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ይህንን ያሉት የኢፌዲሪ ባህር ኃይል የማዕረግ፣ የአርማ፣ የደንብ ልብስና የመሠረታዊ ባህረኞች ማሰልጠኛ ማዕከሉ ግንባታ በቢሾፍቱ ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው።

ኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው የተነሱበት ወቅት ላይ እንገኛለን ያሉት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ፣ እነዚህ ጠላቶች አገሪቷን በማዳከም ከችግር እንዳትወጣ፣ ታላቅነቷን አስጠብቃ እንዳትሄድ እየሰሩ ነው ብለዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች የሚፈጠሩትን ግጭቶች ሰራዊቱ በየቦታው እየሄደ እያመከነ ይገኛል ነው ያሉት።

ይህ ሁሉ ትንኮሳ፣ ማናቆርና ህብረተሰቡን እርስበርሱ ማባላት ኢትዮጵያን ለማዳከም ነው ሲሉ ተናግረዋል። ፍላጎቱም አገሪቷ ስትዳከም ባላት ሃብት እንዳትጠቀም ማድረግ ነው ብለዋል።

ከ100 ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚሰሩ ኃይሎች ዛሬ ተጠናክረው በሀገሪቱ ላይ ዘምተዋል ያሉት ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ፣ ባንዳዎችን ይዘው አገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱ ያሉትን እነዚህን ኃይሎች በውጭ ወራሪ እንደማንቻል ስለሚያውቁ ከውስጣችን ሊያፈራርሱን ያስባሉ ብለዋል።

ህዝቡ ከሰራዊቱ ጎን በመቆም የተደገሰውን ለማክሸፍ መታገል ይኖርበታል ሲሉም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያን ለማዳን ሁላችንም አንድ መሆን ይገባናል፤ተሳስተው የጠላት መሳሪያ የሆኑ አካላትም ቆም ብለው ማሰብ እንደሚገባቸውና ለሃገራቸው ጥፋት እየደገሱ ለሌሎች ታሪካዊ ጠላቶች በር መክፈት የለባቸውም ነው ያሉት።

ሰራዊቱም ደግሞ ኢትዮጵያን ለመጠበቅ በቁርጠኝነት እንደሚሰለፍና ኢትዮጵያ ወደፊት እንደምትራመድ ይህንንም ችግር እንደምትሻገር አስረድተዋል።

ህብረተሰቡም  ኢትዮጵያን ለመጠበቅና ከውጭ ወራሪዎች ለመከላከል አንድ ሆኖ እንዲቆም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።